የቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራርና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ

149

መስከረም 23/20215 /ኢዜአ/ የቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራርና ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውንና ከ360 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሰራዊት አበረከቱ።

የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች "ደማችን ለሰራዊታችን በሚል መርህ" የደም ልገሳም አድርገዋል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አዳኦ ፈጆ፤ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ጀግና ሰራዊት መደገፍና ደም መለገስ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራርና ሰራተኞች በዛሬው እለት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ከመደገፍ በተጨማሪ የተለያዩ የአይነት ድጋፎችን ማድርጋቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም 360 ሺህ ብር ግምት ያላቸው አልባሳት እና 82 ሺህ ብር የሚያወጡ የእርድ እንስሳትን አበርክተናል ብለዋል።

ለሰራዊቱ አለኝታነታችንን ለማሳየት የደም ልገሳ መርሃ ግብር አከናውነናል ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይም በዚህና መሰል ድጋፎች ላይ በመሳተፍ አጋርነታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በደም ልገሳው የተሳተፉ የሆሰፒታሉ ሰራተኞች በበኩላቸው መከላከያ ሰራዊትን መደገፍ አገር ላይ የመጣን ጠላት በጋራ መመከት በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአገር ሰላም ለምንም ነገር መሰረት በመሆኑ ለአገር ህልውና እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊት መደገፍ ያኮራል ብለዋል።

የአገርን ህልውና የመጠበቅ ሃላፊነት የሰራዊቱ በቻ ባለመሆኑ እንደ ጤና ባለሙያ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋም ጭምር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ከመከላከያ ሚኒስቴር ተወክለው ድጋፉን የተረከቡት ኮሎኔል ደሜ ግዛው፤ የቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራርና ሰራተኞች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

''ድጋፍ ያለው ሰራዊት ምንግዜም አሸናፊ ነው'' ያሉት ኮሎኔሉ ህዝቡ የሚያደርገው የትኛውም አይነት ድጋፍ ለሰራዊቱ ''ሞራልም ስንቅም'' ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካጋጠማት ፈተና እስክትላቀቅ ድረስ ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም