በሰባት ክልሎች ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ሰብል እየለማ ነው

129

 መስከረም 23/2015 (ኢዜአ)  በሰባት ክልሎች ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ሰብል እየለማ መሆኑን  የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በክልሎቹ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች በስትራቴጅክ ሰብል ልማቱ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውም ተገልጿል።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን በተለይም አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በማደራጀት በኩታ ገጠም የማረስ ዘዴ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

የአርሶ አደሩን አስተራረስ በማሻሻል ና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ ተኮር የማምረት ሂደትን  እውን ለማድረግ 10 ሰብሎች መመረጣቸውን ጠቅሰዋል።

የተመረጡት ሰብሎችም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ የቢራ ገብስ፣ ሰሊጥ፣ እንዲሁም ከአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ አቮካዶ፣ ማንጎና ብርቱካን ሲሆኑ በሰባት ክልሎች በመተግበር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ከምግብ ፍጆታ ባለፈ አርሶ አደሮች ምርተቻቸውን ወደ ገበያ በማቅረብ የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለዓመታት ሲተገበር የቆየውን የተበጣጠሰ የእርሻ ልማት በመቀየር በኩታገጠም አስተራረስ ትራንስፎርም በማድረግ ካመረቱት ውስጥ 75 በመቶውን ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ የተደራጁ አርሶ አደሮች ሙሉ ግብዓቶችን በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው ሌሎች አርሶ አደሮች በሄክታር ከሚያገኙት አማካይ የምርት መጠን እስክ 40 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ዘመናዊ ግብርና እየገቡ ያሉ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ መጀምራቸውን ጠቅሰዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በመኸር እርሻ ብቻ ሳይወሰኑ ወደ በጋ የመስኖ ልማት እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም