የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደርና ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ የደጀንነት ሚናቸውን እየተወጡ ነው

93

ባህር ዳር (ኢዜአ) መስከረም 23/2015 የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ህዝብን በማስተባበር አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ከመጠበቅ ባለፈ በአሸባሪው ህወሓት የተከፈተውን ጦርነት እየመከተ ላለው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የደጀንነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።

የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባሻ እንግዳው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት በጠላትነት የፈረጀውን የአማራን ህዝብ አንገት ለማስደፋትና ኢትዮጵያን ለመበተን አልሞ እየሰራ ነው።

የሽብር ቡድኑ ባለፈው ዓመት በፈፀመው ወረራ ደብረታቦርን ለመያዝ ቢመጣም በወገን ጦር አከርካሪውን ተመቶ መመለሱን አስታውሰዋል።

ከዛ በኋላም በመንግስት የሰላም አማራጭ ቢቀርብለትም ወደጎን ብሎ የከፈተውን 3ኛ ዙር ጦርነት ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየመከተ መሆኑንና ህብረተሰቡም ስንቅ በማዘጋጀት የኋላ ደጀንነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

"በዚህም እስካሁን ድረስ ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው 124 የእርድ እንስሳት፣ ከ67 ኩንታል በላይ ዳቦ ቆሎ፣ በሶ፣ በርበሬና ሽሮ በከተማው ነዋሪ ተዘጋጅቶ ወደ ግንባር መላኩን" ገልፀዋል።

የከተማው ህዝብ በስንቅ ዝግጅትና ሰርጎ ገቦችን በመከላከል ከሚያደርገው የደጀንነት ተግባር በተጨማሪ ደም በመለገስና በተለያዩ መንገዶች አጋርነቱን እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል።

"አሸባሪው ቡድኑ ታዳጊ ህጻናትና ሴቶችን ጭምር ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑን ጠቁመው፣ "ህዝቡን በማስተባበር የተጀመረው የደጀንነት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ስንቅ ዝግጅት አስተባባሪ ወይዘሮ ብርቱካን ዳምጤ በበኩላቸው፣ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱን በብቃት እንዲመክት ህብረተሰቡ የደጀንነት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።  

አሸባሪው ህወሓት ለ3ኛ ጦርነት ከከፈተ ጊዜ ጀምሮ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሃብቱ እና የከተማው ነዋሪ ህዝብ የእርድ እንስሳትን በማቅረብና በስንቅ ዝግጅት አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በሴትና ወጣት አደረጃጀቶች የተዘጋጀው የስንቅ ዝግጅት በየጊዜው ወደግንባር እየተላከ ሲሆን እስካሁንም 67 ኩንታል ዳቦ ቆሎ፣ በሶ እና ደረቅ ምግብ በማዘጋጀት መላኩን ወይዘሮ ብርቱካን አስታውቀዋል።

"ጦርነቱን ለመመከት የሚደረገው ትግል በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የተጀመረው የደጀንነት ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ አስታውቀዋል።

"ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በግንባር ጠላትን እየተፋለመ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል ማስመዝገብ የሚቻለው የኋላ ደጀንነት ሲታከልበት ነው" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አበባ መንጌ ናቸው።

የአሸባሪው የህወሓት ቡድን እያካሄደ ያለው ጦርነት በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በድል አስኪቋጭ ድረስ በስንቅ ዝግጅት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወይዘሮ አበባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም