ከተለያዩ ቁሶች የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት የሚማርበትን ትምህርት ቤትና የአካባቢውን ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ ያደረገው ታዳጊ

1451

በቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ዌብ ከተማ ከተለያዩ ቁሶች የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት የሚማርበትን ትምህርት ቤትና የአካባቢውን ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ ያደረገው ታዳጊ የፈጠራ ስራዎቹ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተጎበኙ።

May be an image of 8 people and people standing

በቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ዌብ ከተማ የሚኖረው የ16 ዓመቱ ታዳጊ አዳን ሁሴን ዲዳ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን የመስራት ልምድ አለው።

በፈጠራ ስራዎቹ የኤሌክትሪክ ሃይል ከመፍጠሩ አስቀድሞ የተለያዩ ፈጠራዎችን በመስራት የሚታወቅ ታዳጊ መሆኑ በአካባቢው የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ።

ከፈጠራ ስራዎቹ መካከል የተለያዩ ቁሶችን በመጠቀም የኤሌከትሪክ ሃይል በመፍጠሩ ከሚማርበት ቱላ ዌብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  በተጨማሪ በዌብ ከተማ 37 መኖሪያ ቤቶች መብራት እንዲያገኙ አድርጓል።

አዳን ኤሌክትሪክ ማመንጨት የቻለው ከቤትና ከዱር እንስሳት ፍግ፣ ከሰው አይምድር ፣ ጨውና ሌሎች አነስተኛ ቁሳቁሶችን በመጠቀም መሆኑን ይናገራል።

May be an image of 1 person and outdoors

የፈጠራ ስራውን እውን ለማድረግ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን አስታውሶ በ10ኛ ሙከራው የተሳካለት መሆኑን ጠቅሶ በስራውም የሚማርበትን ትምህርት ቤት ጨምሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የፈጠራ ስራው አሁን ባለው ሁኔታ ያለምንም መቆራረጥ ለአምስት ወራት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚናገረው ተማሪ አዳን ከፈጠራ ውጤቱ በወር እስከ 7 ሺህ ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጿል።

May be an image of 4 people, people standing and outdoors

የፈጠራ ውጤቱን ይበልጥ ለማሻሻል እና ከፍ ለማድረግ ሳይንሳዊ ስልጠና ያስፈልገኛል የሚለው ታዳጊው ከአምስት ወራት በኋላ የኤሌክትሪክ ሃይል ግብአቶቹ ላይ እድሳትና ማሻሻያ በማድረግ አገልገሎቱ የሚቀጥል መሆኑን ተናግሯል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ፤ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ እና ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተማሪውን የፈጠራ ውጤቶች ጎብኝተዋል።

የታዳጊውን የፈጠራ ውጤቶች ከጎበኙ በኋላም ያበረታቱት ሲሆን የፈጠራ ስራዎቹ ይበልጥ እንዲጎለብቱ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል።

የፈጠራ ውጤቱን በማስፋት በተለይም በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ገልፆላቸዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በታዳጊው ፈጠራ መደመማቸውንና ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።