በክልሉ በቀጣይ ወራት ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት በትኩረት መከላከል ይገባል –ኢንስቲትዩቱ

417

ባህር ዳር መስከረም 22/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ቀድሞ ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ  ከፍተኛ የወባ ስርጭት ከሚስተዋልባቸው ዞኖች፣ የጤና መምሪያ ሃላፊዎችና የወባ በሽታ ባለሙያዎች ጋር ወባን መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ በባህር ዳር መክሯል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንደገለጹት በምእራብ አማራ የሚገኙ 45 ወረዳዎች የክልሉን 76 በመቶ የወባ ስርጭት የሚሸፍኑ በመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ችግሩን በቀላሉ ለመቅረፍ ያስችላል።

ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን በተደረገ ምርመራ ከ160ሺህ ዜጎች በላይ በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡንም ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቋቋም 3 ሚሊዮን አጎበር በማስገባት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አካባቢን በማጽዳት፣ ያቆረ ውሃን በማፋሰስ ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን በመተግበር ላይ ያተኮረ የመከላከል ተግባር ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራርና የዘርፉ ባለሙያ ህብረተሰቡን ስለበሽታው መከላከያ መንገዶች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት እንደሚጋባቸው ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለወባ ተጋላጭ በመሆኑ 406 ቀበሌዎች የአጎበር እደላና የኬሚካል ርጭት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ምሳ ታረቀኝ ናቸው።

ስጋቱን ለማስቀረት ባለሙያው ህብረተሰቡን የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠርና ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ኪዳት አየለ እንዳሉት የወባ በሽታ ስርጭቱ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።