አልማ የክልሉን የልማት ክፍተቶች በራስ አቅም በመሙላት አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው -- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

157

ባህርዳር፣ መስከረም 22 /2015 (ኢዜአ) የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የአማራ ክልልን የልማት ክፍተቶች በራስ አቅም በመሙላት አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ርዕሰ-መስተዳድሩ ይህን ያሉት ማህበሩ 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውንና የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት በባህር ዳር ከተማ እያከበረ ባለበት መድረክ ላይ ተገኝተው ነው።

አልማ በማህበራዊና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት ላይ በማተኮር የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ርዕሰ-መስተዳድሩ ተናግረዋል።

May be an image of 3 people, people sitting and indoor

ማህበሩ ከአባላት በሚሰብስበው ገንዘብ ለህዝብ ጥቅም የሚሰጡ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ተቋማትን በመገንባት አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።

ማህበሩ ከምስረታው ጀምሮ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሙያ ክህሎት ስልጠናና ሌሎች ተግባራት ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በተለይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲስፋፋ ማህበሩ እያከናወነ ያለው ስራ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልፀዋል።

"የልማት ችግራችንን በዘላቂነት መፍታት የምንችለው አንድ ሆነን በመንቀሳቀስና መደጋገፍ ስንችል ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም የአልማ ፈለግ አዋጭ መንገድ ነው ብለዋል።

ህዝብ የማይነጥፍ የልማት ሃብት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የክልሉ ተወላጆችና የልማት ደጋፊዎች በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ማህበሩን በማገዝ የክልሉ ልማት እንዲፋጠን በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ማህበራዊ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ሁሉም አልማን መደገፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዶክተር ይልቃል ጥሪ አቅርበዋል።

ማህበሩ የክልሉን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ የጀመራቸውን የልማት ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚያደርገው ጥረት የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደማይለየው አስረድተዋል።

May be an image of 1 person and standing

የአልማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ በበኩላቸው ማህበሩ የክልሉ መንግስት የማይገባባቸው የልማት ዘርፎችን ለይቶ በመሙላት ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የልማት ማህበሩ የዛሬ 30 ዓመት በጥቂት ልማት ወዳድና በጎ አሳቢ ግለሰቦች ስራውን ቢጀምርም በአሁኑ ወቅት የአባላቱን ቁጥር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

በየዓመቱም እስከ 1 ቢሊዮን ብር ሃብት በማሰባሰብ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትን ከመገንባት ባሻገር በስራ ዕድል ፈጠራና ገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች እየተሳተፈ ይገኛል።

በዚህም የትምህርት ዕድል ያላገኙ በርካታ ህጻናት የትምህርት ተጠቃሚ መሆናቸውንና ወላድ እናቶችን በአካባቢያቸው በተገነቡ የጤና ተቋማት እንዲጠቀሙ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ ነው ብለዋል።

ለአንድ ቀን እየተካሄደ በሚገኘው የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም የተጓደሉ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢና የስራ አመራር ቦርድ አባላትን በአዲስ ይተካል ተብሎ ይጠበቃል።

በጠቅላላ ጉባኤውም ከ2012-2014 የለውጥ እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የኦዲት ሪፖርትና የቀጣይ ሁለት ዓመታት ስትራተጅክ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድበት ከመርሃ ግብሩ መረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም