የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዲ እሬቻ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ መጠናቀቁን ገለጹ

158

መስከረም 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዲ እሬቻ በዓል ባህልና ወጉን በጠበቀ መልኩ በሰላምና በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የዘንድሮው የእሬቻ በዓል በሰላምና በደመቀ ሁኔታ መከበሩን አስመልክተው ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የምስጋና መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት እሬቻ ባህልና ወጉን በጠበቀና እሴቱን ባጎላ መልኩ ደምቆ እንዲከበር ለረዳን ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ፤ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ጉልህ ሚና ለተጫወቱት አካላትም ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ሽመልስ "የኦሮሞ እና መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በበዓሉ ደምቃችሁ አድምቀችሁናልና ለዚህ ታላቅ ሁነት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና በራሴ ስም ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ" ብለዋል።

"የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ቤት ያፈራውን ይዛችሁ በየመንገዱና በየአዳባባዮቹ የበዓሉ ታዳሚ ወንድሞቻችሁን በታላቅ ክብር ተቀብላችሁ በማስተናገድ ላሳያችሁት ታላቅ ፍቅር ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ" ብለዋል።

የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎችም ደምቆ ለተመመው የበዓሉ ታዳሚ በደማቁ አስተናግዳችኋልና አመሰግናለሁ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ።

እሬቻ ለሁለቱ ከተሞች በኢኮኖሚውም ሆነ በባህሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

ውቡን ባህሎቻችንን ላልተፈለገ ዓላማ ለማዋል ሁሌም የሚተጉ ጠላቶች ምኞታቸው ከሽፏል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የጸጥታ መዋቅሩ ሌት ተቀን ሳይዘናጋ በዓሉ እንዲደምቅ እና የጠላት ምኞት እንዲከሽፍ በማድረጋችሁ የስራችሁ ውጤት ደምቋልና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

እሬቻ ሳይበረዝና ሳይደበዝዝ ወጉና እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ላደረጋችሁ፣ ዛሬም በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ረጅም መንገድ ተጉዛችሁ ለታደማችሁ ህዝባችን፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች 'ገለቶማ' ልላችሁ እወዳለሁ በማለት ምስጋና አቅርበዋል።

የእሬቻ በዓል አከባበር መስህብ ይሆን ዘንድ የዓለም ማህበረሰብ እንዲያውቀው ላደረጋችሁና አይተኬ ሚና ለተጫወታችሁ የሀገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ተቋማት በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም