በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

286

መስከረም 22 /2015 (ኢዜአ) በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በባህርዳር ስታዲየም ይደረጋሉ።

ከቀኑ 7 ሰአት ድቻ ስፖርት ክለብ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ የብሔር እና የሃይማኖት ስያሜ ያላቸው ክለቦች ስያሜያቸውን እንዲቀይሩ ባወጣው መመሪያ መሰረት ወላይታ ድቻ ስሙን “ድቻ ስፖርት ክለብ” በሚል መለወጡ ይታወቃል።

ሌላው የዛሬ ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰአት ሐዋሳ ከተማና በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚሳተፈው ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ይጫወታሉ።

ትናንት በተደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ መድንን 7 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

ነገ ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 7 ሰአት እንዲሁም መቻል ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 10 ሰአት ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር ይጠናቀቃል።