የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ

290

ደሴ፣ መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዋና ክፍል ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ተስፋዬ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ክብረ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር በቅንጅት ተሰርቷል።

በተደረገ ቅንጅታዊ እንቅስቃሴም በበዓሉ የታደሙ ምዕምናን በዓሉን ያለስጋት በሰላምና በድምቀት ማክበራቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እንግዶች ወደ መጡበት አካባቢ መመለስ መጀመራቸውን ጠቁመው፤ “በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል” ብለዋል።

በበዓሉ የተሳተፉ ምዕምናን በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ትብብርም ምስጋና አቅርበዋል።

በዛሬው የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል በርካታ እንግዶች ታድመውበታል።

ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ በመሆኑ በዓሉ በየአመቱ መስከረም 21 ቀን በድምቀት ይከበራል።