የዩኒቨርሲቲው መምህራን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከስኬት እስኪበቃ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

192

ሰመራ መስከረም 21 ቀን 2015 የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከስኬት እስኪበቃ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

”የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ሚና” በሚል በመሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በመሠራ ዩንቨርስቲ ተካሄዷል።

በዚሁ መድረክ ላይ የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ የተመለከተ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚሁ ወቅት የሰመራ ዩንቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ኡመር አብዱልቃድር እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያን ችግር የሚያቃልል መሆኑን አስታውስዋል።

”የግድቡ ግንባታ ለዘመናት አንገታችንን ካስደፋን ድህነት ለመላቀቅ የምናደርገው ትግል ማሳያ ነው” ብለዋል።

የሠመራ ዩንቨርስቲ ማህበረሰብም በመማር-ማስተማር ሂደቱና በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቹ ሀገራዊ ልማቱን የሚያግዙ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በመከወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ከሚያካሄደው መደበኛ ስራው ጎን ለጎን የግድቡ ግንባታ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ድርሻውን እንደሚወጣም ገልጸዋል።

ዩኒቨርስቲው በውሃ ሃብት ልማት መስክና በዲፕሎማሲው እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የተሻለ እውቀት ያላቸው ዜጎች ለማፍራት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የዩንቨርስቲው ምሁራንም በእውቀት ላይ የተመሠረቱ ጽሁፎችና ጥናቶችን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በመስራት ሀገራችንን አየተከተለች ያለችውን ፍትሃዊ አቋም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅም ሰራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

የዩንቨርስቲው የውሃ ምህንድስና መምህር አቶ አቡዱልወሃብ አቤ በበኩላቸው ሀገራችን የህዳሴ ግድቡን አየገነባች ያለችው ሀገራዊ የሃይል አቅቦት ፍላጎቷን ለማሻሻል መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ይህ በሚገባ በሳይንሳዊ መንገድ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብ ከምሁራን የሚጠበቅ ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
እሳቸውም በቀጣይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማዘጋጀት ሃላፊነታቸውን ከመወጣት በተጨማሪ ሀገሪቱ ያላትን ውሃ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት እንደሚሰሩ ገልጿል።

የህዳሴ ግድቡ የሀሉም ዜጎች የጋራ ሃብትና ተስፋ የሆነ ፕሮጀክት በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም በህዳሴ ዙሪያ የተለያዩ ዲጅታል ሚዲያዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ መብቶች ለማስተዋወቅም ሁሉም ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አንስተዋል።