“ሆራ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓል አከባበር ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ደምቆ የታየበት ነው—ከንቲባ አዳነች አቤቤ

268

መስከረም 21/2015 (ኢዜአ)  “ሆራ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓል አከባበር ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ደምቆ የታየበት እንደነበር የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ የመዲናዋ ነዋሪዎች በዓሉ በሰላም እንዲከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከንቲባዋ ከበዓሉ መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በበዓሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በርካታ ታዳሚዎች የተሳተፉበትና ሰላማዊ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ ባማረ ድባብ፣ በከፍተኛ ድምቀትና ውበት ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ መከበሩን  ነው ያስታወቁት።

“በዓሉ ትብብራችን ጎልቶ የወጣበትና ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ደምቆ የታየበት ነው” ብለዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያዊያን እንድነት ይበልጥ እየተጠናከረ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

በኃይል እኩይ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሞክረው ያልተሳካላቸው የሽብር ቡድኖች በዓሉን ሽፋን በማድረግ በመዲናዋ ሁከት ለመፍጠር የያዙት እቅድ በሰላም ወዳዱ ሕዝብ፣ በጸጥታ ኃይሉና አመራሩ ቅንጅት ሊሳካ አለመቻሉን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለማጠልሸት የሚፈልጉ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች  ጥቃቅን እንከኖችን በመፈለግ የአገር ገጽታ ለማበላሸት የያዙት ውጥን አለመሳካቱንም ገልጸዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪዎች በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከማድረግ ባሻገር ከተማዋን ከማስዋብ እና አካባቢን ከማፅዳት ጀምሮ በየአካባቢው እንግዶችን ባማረ መስተንግዶ መቀበላቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህ ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

አባገዳዎች፣ ሀዳ ሲንቄዎች እና ፎሌዎች  በዓሉ እሴቱንና ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦም ከንቲባ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር የመጡ እንግዶች ወደየመጡበት አካባቢ እስኪመለሱ ድረስ በጀመሩት አግባብ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡