የግሸን ደብረ ከርቤ በዓልን እና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው—የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ

373

ደሴ (ኢዜአ) መስከረም 21/2015 የግሸን ደብረ ከርቤ በዓልና የአካባቢውን ሀብቶች በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻና ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ሥፍራ የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ነው።

የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደሉት፣ በክልሉ ለቱሪዝም መስህብነት የሚውሉ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሮ ጸጋዎች አሉ።

ይሁን እንጂ በመሰረተ ልማት ተደራሽ አለመሆን፣ ቅርሶችን በአግባቡ ባለማስተዋወቅ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በጸጋዎቹ የህዝቡን ዘላቂ ጥቅም ማረጋገጥ አልተቻለም።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያሉ የመስህብ ሃብቶችን በማጥናት፣ በመለየትና በማልማት እንዲሁም ተገቢውን የማስተዋወቅ ሥራ በመስራት ህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በየዓመቱ የሚከበረው የግሸን ደብረ ከርቤ በዓልና በአካባቢው ያለውን የመስህብ ሃብት በአግባቡ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በማሟላት የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንደሚሰራም ነው አቶ ጣሂር ያመለከቱት።

“የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል ዛሬ በድምቀትና በሰላም መከበሩ ምዕመኑን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብና ሌሎች አጋር አካላትን በማስተባበር ቦታውን ለማልማት መልካም እድል ይፈጥራል” ብለዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው፣ “ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ፈተናዎች ቢገጥማትም ተቋቁማ የህዝቦቿን አንድነት በማስጠበቅና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ዛሬ ላይ መድረሷን ገልጸዋል።

“ዛሬም እንደሀገር የገጠመውን ፈተና ተቋቁሞ የጠላቶችን ሴራ ለማክሸፍና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ከአባቶቻችን የወረስነውን የጀግንነት፣ የቁርጠኝነትና የአብሮነት እሴት ማጠናከር ይገባል” ብለዋል።

“በኢትዮጵያ ትብብርና አንድነት ነግሶ፤ የሰዎች ጉዳት ተወግዶና ብልጽግና ተረጋግጦ የተስፋውን ብርሃን የምናይበት ዘመን እንዲመጣ ጠላቶችን በአንድነት ልንመክት ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ላስተባበሩ ሁሉ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ግዛቸው፣ የክልሉ የቱሪዝም ሀብቶች ለምተው የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

“ወሎ የሰላም፣ የፍቅርንና የመቻቻል ባህልና እሴት ጎልቶ የሚታይበት ብቻ ሳይሆን የበርካታ የቱሪስት ሀብቶች መገኛ አካባቢ ጭምር ነው” ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት በአካባቢው ያሉ የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል።

የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ የተከበረው በአካባቢው ሰላም በመኖሩ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡ ለሰላሙ ሁሌም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል።  

በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት መክቶ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረትም መላ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ የበኩሉን እንዲዋጣ አስገነዝበዋል።

በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀትና በሰላም በመከበሩ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ከደብረ ብርሃን ከተማ የመጡት አቶ ብርሃኑ ይልማ ናቸው።

ወደ አካባቢው ለሚመጡ ምዕመናን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለዚህም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌና የሶማሌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስና ሌሎች የመንግስት ሥራ ሃላፊዎችና እንግዶች በበዓሉ ታድመዋል።