የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነ የጋራ እሴት ነው- ከተለያዩ ብሔረሰብ የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች

309

መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነ የጋራ እሴት መሆኑን ከተለያዩ ብሔረሰብ የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ፡፡

የምስጋና፣ የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የሰላም እና የወንድማማችነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎች ከሌሊት ጀምሮ እርጥብ ሣር በመያዝ እንዲሁም የበዓሉ መገለጫ በሆኑ ባህላዊ አልባሳት ደምቀውና ባህላዊ ዜማዎችን እያሰሙ “ሆራ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓልን አክብረዋል፡፡

በበዓሉ የታደሙ የተለያዩ ብሔረሰብ አባላትም ኢሬቻ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የሰላም በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ከታደሙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲዳማ እና የጋሞ ብሔረሰብ አባላት በዓሉ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነ የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

የሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑት አቶ ዳዊት ዳንጌሶ የወንድማማችነት መገለጫ በሆነው የኢሬቻ በዓል በመታደማቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡

የበዓሉ አከባበርም ሰላም፣ፍቅርና ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት የታየበት መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

”ኢሬቻ የመላ ኢትዮጵያዊያን እሴት ነው” ያሉት አቶ ዳዊት፤ ከዚህ አኳያ በዓሉን ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መንገድ በጋራ ልናከብረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የጋሞ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑት አቶ ሙናዬ ሞሰሌ በበኩላቸው፤ የኢሬቻ በዓልን በጋራ ማክበራችን የእርስ በርስ ትስስራችንን  የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ይህም የጥላቻና ግጭት አጥርን በማፍረስ የወንድማማችነት ድልድይን ለመገንባት ያስችለናል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያዊያን አብሮነት መጠናከር ደግሞ የአገር አንድነትንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ኢሬቻ አንድነትን የሚያጠናክር፣  ሰላምን የሚሰብክ፣  እና የፍቅር በዓል ስለሆነ በጋራ አክብረነዋል ያሉት ደግሞ የጫንጮ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቦረና ጌሪ ናቸው።

በበዓሉ ላይ የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መታደማቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያዊያንን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በግልጽ ያመላክታል ብለዋል፡፡