የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነው

161

ደሴ (ኢዜአ) መስከረም 21/2015 በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ የሚገኝበት የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

በንግስ በዓሉ ላይ የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ፣ የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮንን እንደገለጹት በዞኑ ካሉ ባህላዊ፣ ሃይማታዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች መካከል የግሸን ደብረ ከርቤ አንዱ ነው።

በዓሉ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የቅደመ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመው፣ በዛሬው የበዓል አከባበርም በርካታ ምዕመናንና የመንግስት አመራሮች መገኘታቸውን ገልፀዋል።

በዓሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮናቫይረስ መከሰትና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በሚፈለገው ልክ አለመከበሩን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ዘንድሮ ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በልዩ ድምቀት እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ መስፍን እንዳሉት "ግሸን ደብረ ከርቤ ከሃይማኖታዊ በዓሉ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ በመሆኑ ይህን እድል ለቱሪዝም ዘርፉ በስፋት ለመጠቀም ሰፊ ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ከአዲስ አበባ ከተማ የመጡት አቶ መስፍን አበራ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮናቫይረስና ህወሓት በከፈተው ጦርነቱ ምክንያት በበዓሉ መታደም እንዳልቻሉ ገልዋል።

"ዘንድሮ አካባቢው ሰላም በመሆኑ በግሸን ደብረ ከርቤ ተገኝቼ በዓሉን እያከበርኩ ነው፤ በዓሉን እንደበፊቱ ተሰባስበን በሰላም ማክበር በመቻላችንም ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።

በቀጣይም በየዓመቱ ወደስፍራው በመምጣት በዓሉን የማክበር ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ዛሬ እየተከበረ ባለው የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምዕምናን መሳተፋቸውን ከዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም