በደቡብ ወሎ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው

173

ደሴ መስከረም 21/2015 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረትና ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስቀመጠውን   ግብ ለማሳካት  ዞኑ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል።

ቀደም ሲል በልማቱ  የተገኘውን  ልምድ በመቀመር  ዘንድሮው  ከ90 ሺህ  በላይ  አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ በማልማት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።፡

የስንዴን ምርታማነት ለማሳደግም የምርጥ ዘር የማዳበሪያና ሌሎች የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በአግባቡ ከማቅረብ ባሻገር አዳዲስ ቴክኖሎጅና አሰራሮች ይተገበራሉ ብለዋል።

በመስኖ የሚለማውን መሬት በመለየት በተፈጠረው ተከታታይ መድረክ ከአርሶ አደሮቹ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው ሁሉንም  የውሃ አማራጮች ለመጠቀም ጥረት እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በዞኑ ለጋምቦ ወረዳ የ020 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቢላል ሙሄ በሰጡት አስተያየት  በመኸርና በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት በመንግስት ለተቀመጠው ግብ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በበጋው ወራት አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ስንዴ  በማልማት  ተጨማሪ  ገቢ ለማግኘት በዝግጅት  ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በቅደላ ወረዳ የ012 ቀበሌ አርሶ አደር በላይ ሞላ በበኩላቸው አምና ሩብ ሄክተር መሬት በመስኖ ስንዴ አልምተው ከ10 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከአምናው ልምድ በመነሳትም ዘንድሮ ከግማሽ ሄክታር በላይ ማሳቸውን በስንዴ በማልማት ከ25 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን በክረምቱ  ከ172 ሺህ  ሄክታር  በላይ ማሳ  ከለማው  ስንዴም  ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም