አሸባሪው ህወሃትን ለማስወገድ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እናደርጋለን - የትግራይ ክልል ተወላጆች

196

ሀዋሳ፤ መስከረም 20/2015(ኢዜአ) ፡- ሀገርና ህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል እየሰራ ስልጣኑን ለማራዘም ጦርነት የከፈተውን አሸባሪ የህወሃት ቡድንን ለማስወገድ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች አስታወቁ ።

በሀዋሳ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት የከፈተው አሸባሪው ህወሃትን እየመከተ ለሚገኘው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሚደረገው ድጋፍ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተወላጆቹ በውይይት መድረኩ ተናግረዋል።

አሁንም ከመከላከያና ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር ይህንን ቡድን እንደሚታገሉ ነው በሰጡት አስተያየት ያረጋገጡት ፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች  መካከል ሳጅን ገብረኪሮስ ሞገስ፤አሸባሪው  ህወሃት ለሥልጣኑ ሲል ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ እንኳ የማይራራ የአውሬነት ባህሪ ያለው ቡድን ነው ብለዋል ፡፡

ይህም የትግራይን ክልል ነዋሪዎች ሕይወትና ንብረት ሲጠብቅ የኖረን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከጀርባው በማጥቃት ማረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡

ቡድኑ ለስልጣኑ ሲል የደሀውን ልጅ ለጦርነትና ለረሀብ እየዳረገ እንደሚገኝ የአደባባይ ሚስጢር መሆኑን አመላክተዋል።

ነዋሪው የእርዳታ እህል እንኳ የሚደርሰው ልጁን ለጦርነት ከላከ  ብቻ እንደሆነ ያወሱት  ሳጅን ገብረኪሮስ ፤ ይህንን ቡድን የሚደግፍ ለኛም ጠላት  ነው ብለዋል ፡፡

ይህንን የሽፍታ ቡድን  ተባብረን ማውገዝና መታገል ይጠበቅብናል  ነው ያሉት ፡፡

መምህር ሐጎስ መስፍን በበኩላቸው፤  የትግራይ ክልል ህዝብ ጥንትም ጀምሮ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ለሀገሩ ክብርና ሉአላዊነት መስዋዕትነትን ሲከፍል የኖረ ነው ብለዋል ፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የትግራይን ክልል ህዝብ በተደጋጋሚ ለጦርነት እየዳረገ መሆኑን አውስተው፤ እናቶች ልጆቻቸውን ወደ እሳት ከመማገድ ባለፈ ያኔም አሁንም ከዚህ ቡድን ያገኙት አንዳች ጥቅም እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የሽብር ቡድን የተደቀነውን ፈተና ከመከላከያ ጎን ቆመን በመረባረብ ማክሰም ይኖርብናል ብለዋል መምህር ሐጎስ፡፡

በዚህ ጨካኝና ሽፍታ ቡድን ተጨቁነው ላሉት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያዊያን ሠላም ሲባል ቡድኑን ታግሎ ለማስወገድ የበኩላቸውን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

የስልጣን ጥማት ያለበት የሽብር ቡድኑ በከፈተው  ጦርነት ህዝብ ለሞት፣ ለረሀብና ለስቃይ  እንደተዳረገ  የገለጹት ደግሞ አቶ አለም ምሩፅ ናቸው።

ቡድኑ በህዝብ ስም ይነግድ እንጂ ለህብረተሰቡ የማይጨነቅ አረመኔ  በመሆኑ እንጂ  ለመከራ የዳረገውን ህዝብ ለመታደግ ራሱን ለህግ አሳልፎ መስጠት በተገባው ነበር ብለዋል ፡፡

ሀገርና ህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለውን ወንጀል እየሰራ ስልጣኑን ለማራዘም በእብሪት ተነሳስቶ ዳግመኛ ጦርነት የከፈተውን አሸባሪ ቡድን ለማስወገድ በሚካሄደው እንቅስቃሴ በመሳተፍ  ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው  ተወላጆቹ  ያስታወቁት።

በውይይቱ መድረክ  የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ፤ አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያ መከታ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን በማጥቃት ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት የነበረውን የዘመናት ዕቅድ ገሃድ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ሀገርና ህዝብ የካደው ይህ መሰሪ ቡድን ኢትዮጵያን የማዳከም ግቡን ያሳክልኛል ብሎ ያለመውን ጦርነት ማስጀመሩን አስታውሰዋል ፡፡

በዚህም ሊነገር የማይችልና ታሪክ ይቅር የማይለውን ወንጀል በዜጎቻችን መፈጸሙንና በመፈጸም ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የትግራይ ክልል ህዝብን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጦርነት ወዳድ ቡድን ምክንያት እየደማ መቀጠል የለበትም ያሉት አቶ አብርሀም፤  ቡድኑን ከህዝብ ጫንቃ ላይ አውርዶ ለመጣል የክልሉ ነዋሪና ተወላጅ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

በሲዳማ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ይህን የሽብር ቡድን በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር መታገልና የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱትን በመጠቆም  የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ አሸባሪውና ሽፍታው የህወሃት ቡድን አድጎ በጃጀበት የሴራ ፖለቲካ የትግራይ ክልልን ህዝብ ከወንድም ህዝቦች ጋር በጥርጣሬ እንዲተያይ ብዙ መጣሩን አውስተዋል፡፡

ይህ የሁሉም ጠላት የሆነው ቡድን የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያዊያን  ጋር ተባብሮ በመታገል ሴራውን ማክሸፍና በቃህ ሊለው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ሠላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተወላጆቹም ለጋራ ሀገራዊ ሠላም መስፋን ከሌሎች ህዝቦችና ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብረው እንዲሰሩም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም