የፍትህ አካላት አሸባሪውን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ በመልሶ ግንባታው የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል—ፍትህ ሚኒስቴር

208

ደብረ ብርሀን መስከረም 20/2015 (ኢዜአ) -የፍትህ አመራሮችና ባለሙያዎች አሸባሪው ህወሓትና ተባባሪዎቹን በህግ ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራ በንቃት እንዲሳተፉ የፍትህ ሚኒስቴር አሳሰበ።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ “እኛ ዐቃብያነ ህግ ለህግ፣ ለፍትህና ለርትዕ እንሰራለን” በሚል መሪ ሃሳብ ያለፈውን ዕቅድ አፈፃፀም የሚገመግምና የ2015 ዕቅዱን የሚያስተዋውቅ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው።

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓትና ተባባሪዎቹ በንጹሀን ዜጎች ላይ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የንብረት ዝርፊያና የውድመት ወንጀል ፈጽመዋል።

ይህም በህዝብ ላይ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ የጤናና ስነ ልቦና ችግሮችን ማስከተሉን አስታውሰው፣ ይሄን ችግር ለማስወገድ ዐቃቤ ሕጎች ተግተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

“የሽብር ቡድኑ የፈፀማቸው ወንጀሎች ተደብቀው እንዳይቀሩና አሁንም ህወሓት የጠነሰሰው ሴራ እንዳይሳካ ዐቃቤ ሕጎች ወንጀሎችን በአግባቡ መርምረው ለህግ በማቅረብ በኩል የሚያኮራ ተግባር አከናውነዋል” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጠንክረው እየሰሩ  ያሉበት ወቅት ላይ ነን” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የፍትህ አካላት ችግሩን ተረድተው ማህበረሰቡንና መንግስትን በላቀ ሙያዊ ስነምግባር ሊያገለግሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተገፉ ንጹሀንን በህግ ለመካስ ከሚያደርጉት ትግል ባሻገር በጦርነቱ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ገረመው ገብረፃድቅ በበኩላቸው፣ ፍትህ ሚኒስቴር አሸባሪው ህወሓት በክልሉ የፈጸመውን ወንጀል አጣርቶ የዓለም ህዝብ እውነታውን እንዲያውቀው በማድረግ በኩል ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

“በቀጣይ ከሚኒስቴሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ለህግ የበላይነት መከበር በትኩረትና በትብብር እንሰራለን” ሲሉም አክለዋል።

ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ያለው መድረክ የ2014 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ ላይ ያተኮረ ነው።

በክልሉ የሚገኙ የፍትህ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ዐቃቤ ህጎች፣ ፖሊስ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በመድረኩ መሳተፋቸው ታውቋል።