ኢሬቻ አንድነትን ፣ አብሮነትን እና መተባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው

174

ሐረር መስከረም 20/2015(ኢዜአ) ኢሬቻ አንድነትን ፣ አብሮነትን እና መተባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል መሆኑን የሐረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ገለጸ።

የሐረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነት እና የአንድነት ማሳያ ለሆነው የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፏል።

የክልሉ መንግሥት በመልካም ምኞት መግለጫው እንደገለጸው፤ ኢሬቻ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሀብት ከመሆኑም ባሻገር አንድነትን ፣ አብሮነትን እና መተባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው።

የክልሉ መንግሥትም ካለፉት አራት አመታት ወዲህ የኦሮሞን ባህል፣ እሴትና ታሪክን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጾ፤በተለይ ኢሬቻን በሚመለከት ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክቷል ።

በመሆኑም የኢሬቻ በዓልን ስናከብር ባህልና ወጉን በጠበቀና በሚያጠናክር መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ሊሆን ይገባል ሲልም አመልክቷል።

የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎችም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን እና ወንድማማችነትን በማጎልበት ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ ያቀርባል።

የኢሬቻ በዓል እንደወትሮው ሁሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነት እና የአብሮነት በዓል እንዲሆን የክልሉ መንግስት ከልብ ይመኛል ብሏል በመግለጫው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም