በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የእንሰሳት መኖ ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ ገባ

194

ባህር ዳር መስከረም 20/2015(ኢዜአ) በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በ1 ነ ጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ በወር ከ125 ሺህ ኩንታል በላይ የእንሰሳት መኖ ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱ ተገለጸ።

ፋብሪካው ምርቱን በቀጥታ ለተጠቃሚው አርሶ አደር ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የሚያግዝ የባለድርሻ አካላት ውይይት በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት የመኖ ልማት ባለሙያ አቶ አበበ ምትኬ እንዳሉት በክልሉም ሆነ በሃገሪቱ ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር ቢኖርም በምርታማነት ዝቅተኛ ነው።

የተመጣጠነ መኖ እጥረት መኖሩ የእንስሳት የስጋ፣ የወተት፣ የእንቁላልና መሰል ምርቶችን በበቂ መጠን ለማምረት አዳጋች አድርጎታልብለዋል።

በክልሉ ያለውን የእንስሳት የመኖ ፍላጎት ለማሟላት ከ45 ሚለዪን ቶን በላይ ድርቆሽ መኖ የሚያስፈልግ ቢሆንም እየቀረበ ያለው ለምርታማነት ዝቅተኛ ጠቀሜታ ያለው ከ40 ሚሊዮን ያልበለጠ ነው ብለዋል።

በተለይም በአብዛኛው እየቀረበ ያለው የሰብል ተረፈ ምርት በመሆኑ የእንስሳት ምርታማነት ለማሳደግ በቂ አለመሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ 18 የሚደርሱ የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ቢኖሩም በጥራት ችግርና በማምረት አቅም ክፍተት አብዛኞቹ የሚፈለገውን ያህል አስተዋጽኦ እያበረከቱ አለመሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑም በባህር ዳር ከተማ የተገነባው የሙሌ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ችግሩን ለመቅረፍ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በኤም.ኤስ.ኤ ቢዝነስ ቡድን የሙሌ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሙሉዓለም አለነ በበኩላቸው ፋብሪካው የእንስሳት መኖ እጥረት በመፍታት ምርታማነትን ለማሳደግ የተገነባ ነው ብለዋል።

ኢትዮጲያ በእንስሳት ቁጥር ግንባር ቀደም ሃገር ብትሆንም በምርታማነት ግን እጅግ ዝቅተኛ መሆኗን ጠቅሰው፤ ለዚህም የተቀነባበር መኖ እጥረት በመኖሩ እንደሆነ ገልፀዋል።

ችግሩን አቅም በፈቀደ ለመፍታት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበትና በቀን 4 ሺህ 800 በወር ከ128 ሺህ ኩንታል በላይ የተቀነባበረ መኖ ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ወደ ስራ ማስገባታቸውን ተናግረዋል።

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለ250 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም ከ700 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ፋብሪካው በ18 ወራት ተጠናቆ ወደ ማምረት መግባቱን አመልክተው፤ የምርት አቅርቦቱን ከሃገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱንም አብራርተዋል።

በዞኑ የጎጃም ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የተገነባ ቢሆንም አርሶ አደሩ ባለበት የተመጣጠነ መኖ አቅርቦት የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ምርት ማግኘት እየተቻለ እንዳልሆነ የገለፁት ደግሞ የምስራቅ ጎጃም ዞን ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙሉቀን ቢያድግልኝ ናቸው።

ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ ደረጃውን የጠበቀ መኖ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ለዚህም ይህ ፋብሪካ ችግሩን ያቃልላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል

።በመድረኩ በክልሉ የተውጣጡ የመኖ ባለሙያዎችና የህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም