በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ሁለት ተቋማት ከ15 ሚሊዮን በሚበልጥ ወጪ መልሰው ተገነቡ

94

ደሴ (ኢዜአ) መስከረም 20/2015 በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አሸባሪው ህወሓት ያወደማቸውን ሁለት ተቋማት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ መሀመድ አሚን የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ በፈጸመው ወረራ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑ በከተማዋ በወረራ በቆየበት ጊዜ 95 ንጹሀንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ 46 ዜጎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት በማድረስና 49 ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግስትና የህዝብ ሃብት በመዝረፍና በማውደም ህብረተሰቡን ለችግር ማጋለጡን ነው ከንቲባው የገለጹት።

በአሸባሪው ህወሓት ዝርፊያና ውድመት የደረሰባቸው የሀሮ አገር መጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አንድ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም መልሰው ተገንብተው ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስረድተዋል።

አቶ መሀመድ እንዳሉት፣ ዛሬ የተመረቁትን ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጓል።

ተቋማቱ በ3 ወራት ብቻ መገንባታቸውን ገልጸው፣ "ይህም ፕሮጀክትን ፈጥኖ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ልምድ የተገኘበት ነው" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ቀደም ሲል የፈጸመው ግፍና በደል ሳይበቃው አሁንም ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን አስታውሰው፣ ጦርነቱን ለመመከት በሚደረገው እንቅስቃሴ የኮምቦልቻ ከተማ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር የደጀንነት ሚናውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

የሀሮ አገር መጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህር ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ካሳሁን መሀመድ በበኩላቸው፣ "ትምህርት ቤቱ በህወሓት ታጣቂዎች ቢወድምም መልሶ በተሻለ ደረጃ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል" ብለዋል።

በመልሶ ግንባታው 12 መማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ዛሬ ለአገልግሎት በመብቃታቸው አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በተሻለ ለመተግባር ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።

ከኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አያሌው ሁሴን በሰጡት አስተያየት የሽብር ቡድኑ ያደረሰው የሰብአዊና ቁሳዊ ሃብት ውድመት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።

"መንግስት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተቋማቱን መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት በማብቃቱ ተደስተናል፤ እናመሰግናለን" ያሉት አቶ አያሌው፣ ሕብረታችንን በማጠናከር አሸባሪው ህወሓት ለ3ኛ ግዜ የከፈተውን ጦርነት በጋራ እንመክታለን ብለዋል።

በተቋማቱ የምርቃ ስነ ስርዓት ላይ የከተማው አመራሮች፣ የህብረተሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም