''አትዮጵያ ሙሉ የምትሆነው የሕዝቦች ባህልና ማንነት እኩል መከበር ሲችል ነው'' -- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

186

መስከረም 21/2015-----"አትዮጵያ ሙሉ ሆና የምትታየውና የምትጎላው የሕዝቦች ባህልና ማንነት እኩል መከበር ሲችል ነው'' ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ሆራ ፊንፊኔ የሕዝቦችን አንድነት ከማስተሳሰር ባለፈ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

አራተኛው የኢሬቻ ፎረም አባገዳዎች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮችና ሌሎች አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በዚሁ መድረክ ላይ ፕሬዚዳንቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኢትዮጵያ የምትጎላው የሁሉም ባህል እንዲታይ ሲደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

''የአንዱ ባህል ከጎደለ አገር ሙሉ አትሆንም'' ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ባህልና ታሪኩ የማይከበርለት ሕዝብ ደግሞ ውጤታማ አይሆንም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ የሚያስረዳው ሕዝቦች በራሳቸው ባህልና ማንነት ብዙ ችግሮችን ሲፈቱ እንደነበር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

"ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ ሙሉ ሆና እንድትታይ የሁሉም ሕዝቦች ባህልና ማንነት በእኩልነት ሊከበር ይገባል" ብለዋል።

አቶ ሽመልስ እንዳሉት የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ማንነት ሲገለጽበት የኖረ የአደባባይ በዓል ነው።

በዓሉ ባለፉት አራት ዓመታት በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እየተከበረ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህም የሕዝቦችን አንድነት ያስተሳሰረ ክስተት ነበር ብለዋል።

በዓሉ በአዲስ አበባ መከበሩ ለከተማዋ ነዋሪም የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ "የከተማዋ ሕዝብ ከበዓሉ በረከቶች ተካፋይ መሆኑም የሚያስደስት ነው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ኢሬቻ መነሻው የኦሮሞ ሕዝብ ይሁን እንጂ የሁሉም በዓል መሆኑን አንስተዋል።

"የበዓሉ ዋናው ሀሳብ በጥቅሉ ስለ አብሮነት፣ ስለ አንድነትና ስለ መተሳሰብ የሚነገርበትና የሚገለጽበት ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም የኢሬቻ እሴት የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስተሳሰረና አብሮ ያኖረ አሁንም በዚሁ ልክ እየቀጠለ ያለ በዓል መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ኢሬቻ በገዳ ስርዓተ አማካኝነት ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ዓለም ቅርስ የሆነ ዘመን ተሻጋሪ በዓል እንደሆነም አክለዋል።

"ይህም በመሆኑ የኢሬቻ በዓል ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠብቀው፣ ሊንከባከበውና ሊጠብቀው ይገባል" ሲሉ ነው ወይዘሮ አዳነች ያስገነዘቡት።

በመድረኩ ላይ የኢሬቻ ምንነትን የተመለከቱ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል ነገና ከነገ ወዲያ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ የሚከበር ሲሆን በዚህ በዓል ከኬኒያ የሚመጣና የተለያዩ አካላትን የያዘ ልዑክም ተሳታፊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም