የኢትዮጵያንና ደቡብ ኮሪያን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ጉባኤ ተካሄደ

168

መስከረም 20 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የንግድና የኢንቨስትመንት ጉባኤ በደቡብ ኮረያዋ ቡሳን ከተማ ተካሂዷል።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም የኮሪያ-ኢትዮጵያ የንግድ ማህበር በተዘጋጀው የኢንቨስትመንትና የንግድ ጉባኤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር የንግድ ለንግድ ትስስሩን ለመገንባት ያለመ ነው።

በመድረኩ ሽንተስ ኢቲፒ ጋርመንት የተሰኘና በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማራ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ስኬት በኢትዮጵያ ላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንደ ማሳያነት ቀርቧል።

ሌሎች የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲጠቀሙ ተጠቁሟል።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በጉበኤው ላይ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ የሆነ ታሪካዊ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ግንኙነቱ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ትስስር ማደግ ይኖርበታል ብለዋል።

May be an image of 1 person and standing

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስላለው ሰፊ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎች ገለጻ አድገዋል።

በሀገሪቱ የተደረገው ሪፎርም ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተው በኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለ ሀብቶችን ለማገዝ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዋናው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉባኤ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ከሚፈልጉ ደቡብ ኮሪያውያን ባለሀብቶች ጋር የንግድ ለንግድ ውይይቶችም ተደርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም