በኢትዮጵያ እየተከናወነ ላለው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት የትምህርት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም

182

መስከረም 20 / 2015 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ እየተከናወነ ላለው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት የትምህርት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የሰምምነቱ ዋነኛ ዓላማ ትምህርት ቤቶች ዜጎችን በሥነ ምግባር በማነፅ በሀገር ሰላም ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑ ተመላክቷል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በሀገሪቱ ውስጥ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እና በዘላቂነት እንዲረጋገጥ በትውልድ ቅብብሎሸ  ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የትምህርት ተቋማት ሚና ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው፤ ትውልዱን ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እሰከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላምን አስፈላጊነት  በአግባቡ እንዲገነዘብ መቅረፅ ተገቢ ነው ብለዋል።

ዛሬ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረሰው ስምምነትም የትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ በእውቅት የታነጹ እና በምክንያት የሚያምኑ ተማሪዎችን  ማፍራት ከተቻለ የሀገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ የሰላምና የግበረ ገብ እሴቶች ትኩረት እንደተሰጣቸው አንስተው፤ ስርዓተ ትምህርቱ ሲተገበር ተማሪን ከክፍል ወደ ክፍል ለማዛወር ብቻ ሳይሆን ትውልድ ቀረጻ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል።