የኢሬቻ ኤግዚቢሽንና ባዛር የኦሮሞን ባህልና ማንነት የማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሯል

210

መስከረም 19/2015 የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የኢሬቻ ኤግዚቢሽንና ባዛር የኦሮሞን ባህልና ማንነት የማስተዋወቅ ዕድል መፍጠሩን የባዛሩ ተሳታፊዎችና ሸማቾች ገለጹ።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜ በሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ይከበራል።

ለዚሁ በዓል ድምቀት ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቶ ለእይታ ቀርቧል።

በተጨማሪም በኦሮሞ ባህል ማዕከልም የተለያዩ የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት የሚያሳዩና የብሔሩ መገለጫ የሆኑ ቁሶች ባዛር ላይ ቀርበዋል።

በእዚሁ ስፍራ ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ከመጡት መካከል የ'ና ኢፍ' የኦሮሞ ባህል አልባሳት መሸጫ ባለቤት ወይዘሮ ጋዲሴ ታደሰ የባህል አልባሳትን ይዘው በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ መዘጋጀቱ የኢሬቻ ታዳሚዎች በበዓሉ ላይ ባህላቸውን የሚያንጸበርቁበት አልባሳትን በቀላሉ ማግኘት እንደሚያስችላቸውም ጠቅሰዋል።

'ሚቹ ግራፊክስ' ማተሚያ ድርጅት የገዳ ስርዓትን የሚያሳዩና ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ቲሸርቶችንና ሌሎች መዋቢያዎችን ይዘው ቀርበዋል።

የ'ሚቹ ግራፊክስ' አባል ወጣት ቀቤኛ መርጋ እንዳለችው ኤግዚቢሽንና ባዘሩ የኦሮሞን ሕዝብ ባህልና ማንነት ለማስተዋወቅ ይረዳል።

ባዛሩ የኦሮሞን ሕዝብ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጭምር ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው የጠቆመችው።

በኤግዚቢሽንና ባዘሩ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ መገለጫ የሆኑ የተለያዩ አልባሳትና ቁሶችን ሲሸምቱ ያገኘናቸው ሃደ ሲቄ ሳኡዳ ኦሊ እና ሃደ ሲቄ አዳነች ተሾመ ባገኙት ነገር መደሰታቸውን ይናገራሉ።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ የክልሉን የተለያዩ አካባቢዎች የሚያንጸባርቁ ባህላዊ አልባሳት በስፋት እንዳሉ ማየታቸውን መስክረዋል።

ይህም የኦሮሞን ሕዝብ ባህል፣ ማንነትና እሴት በአገርም ውስጥ ይሁን በውጪ ለማስተዋወቅ ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም