የኢሬቻን በዓል ለማደብዘዝና ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ዓላማቸውን ማክሸፍ ይገባል -- አቶ መለሰ ዓለሙ

81

መስከረም 19/2015 (ኢዜአ) የኢሬቻን በዓል ለማደብዘዝና ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ዓላማቸውን ማክሸፍ እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ አስታወቁ።

የኢሬቻ በዓል አከባበር የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ቄሮዎች፣ ሀዳ ስንቄዎች፣ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በልደታ ክፍለ ከተማ በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል ።

የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ኢትዮጵያውያን በዓላቶቻችንን በጋራ ስናከብር የአንድነት እሴቶቻችንም የበለጠ እንደሚጠናከሩ በኢሬቻ ላይ እየታየ ያለው አብሮነት፣ እህትማማችነት እና ወንድማማችነት አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢሬቻ የሰላምና የፍቅር በዓል መሆኑን ጠላቶቻችንም ይረዱታል፤ አንድነታችንና አብሮነታችን ከተጠናከረ የጠላቶቻችንን የመከፋፈል እኩይ ዓላማ ስለማይሳካ በዓሉን ለማደብዘዝና ሰላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ዓላማቸውን ማክሸፍ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶቻችን ተደራጅተን በፍቅር ተቀብለን ማስተናገድ ይገባል ያሉት አቶ መለሰ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር የበዓሉን ገፅታ በመጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀይሉ ሉሌ በበኩላቸው ኢሬቻ የወንድማማችነትና እህትማማችነት በዓል በመሆኑ በዓሉ በሰላም፣ በፍቅር፣ በአብሮነት እንዲከበር መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢሬቻ ከጥንት ጀምሮ በኦሮሞ ህዝብ ሲከበር የነበረ አንድነትን የሚያጠናክር የሰላም እሴት መሆኑን የጠቀሱት የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የኢሬቻ መለያ የሆነውን ፍቅርና ይቅር መባባልን በማጠናከር በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም