በመዲናዋ ከ800 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የዲጅታል መታወቂያ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል--ኤጀንሲው

መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ800 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የዲጅታል መታወቂያ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት ኤጀንሲው በመዲናዋ የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ እንዲሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡

በዚህም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራምና ከአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው እስካሁን ባለው ሂደት ለ870 ሺህ የመዲናዋ ነዋሪዎች የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰው፤ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የአሻራ ናሙና መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ ኤጀንሲው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉትን የዲጅታል መሰረተ ልማት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህም ኤጀንሲው አገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻሉም በላይ መረጃዎችን በተደራጀ አግባብ ለመያዝ እንደሚያግዝ አክለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው በተያዘው በጀት ዓመት የአሰራር ስርዓት፣ የሰው ሃብት አስተዳደር እና የተቋም አደረጃጀት ማሻሻያ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

ኤጀንሲው በ2014 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ደንበኞቹ አገልግሎት መስጠት የቻለ ሲሆን፤ በዚህም 125 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም