በኢትዮጵያ በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ በርካታ ሰዎች ለህልፈት ይዳረጋሉ-- ጤና ሚኒስቴር

390

መስከረም 19/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ በአማካይ በርካታ ሰዎች ለህልፈት ህይወት እየተዳረጉ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ በዓለም ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 31 በመቶው በልብና ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የዓለም ጤና ድረጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ በየዓመቱ በአማካይ 18 ሚሊዮን ሰዎች በልብ ህመም ምክንያት ይሞታሉ።

በዚህም ልብ ነክ በሽታዎች በዓለም ላይ ዋነኛ የሞት መንስኤነት የተቀመጠ ሲሆን በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መምጣታቸው ተመልክቷል።

የዓለም የልብ ቀን "ለሁሉም የልብ የጤና ልብ እንበል" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ በአለም ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ በዛሬው እለት ተከብሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የጤና የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ሩት ንጋቱ፤ በኢትዮጵያ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ዋነኛ የሞት መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ በአማካይ 170 ሰዎች ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 45 በመቶው በልብ የደም ቧንቧ ጥበት፣ 34 በመቶው በስትሮክ እንዲሁም 11 በመቶ በደም ግፊት ለህልፈት የሚዳረጉ መሆኑን ዘርዝረዋል።

ለልብ እና ደም ቧንቧ በሽታዎች ከሚዳርጉ አጋላጭ መንስኤዎች መካከል ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ የደም ግፊት፣ የቤት ውስጥ አየር ብክለት፣ የደም ውስጥ ቅባትና የስኳር መጨመር መሆናቸው በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

የአልኮል መጠጥ ማዘውተርና ሲጋራ ማጨስም ለዚሁ ህመም አይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸው ይነገራል።

በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል የአልኮል መጠጥና ሲካራን መተው እንዲሁም የአመጋገብ ስርአትን ማስተካከል እንደሚገባ በባለሙያዎች ይመከራል።

በገር አቀፍ ደረጃ በሽታውን ለመከላከል ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ሩት ከ300 በላይ የጤና ተቋማት የደም ግፊት ልየታና ምርመራ ህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 7 people, people sitting, people standing and indoor

የዓለም የልብ ቀንን ምክንያት በማድርግም ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በነጻ የደም ግፊት ልኬት እና መሰል አገልግሎቶች የሚሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም