ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያስመዘገበች ያለው ስኬት የልማት ግቦቿን እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው- ምሁራን

121

መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያስመዘገበች ያለው ስኬት የልማት ግቦቿን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የአዲስ አበባ፣ የኦስሎ እና የማላዊ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ አገራት ዘላቂ የልማት ግቦቻቸውን ለማሳካት እያከናወኑ ያለውን ተግባርና እየገጠማቸው ያለውን ተግዳሮት በሚመለከት በአዲስ አበባ ምክክር አካሂደዋል።

በምክክሩም የየዩኒቨርሲቲዎቹ ምሁራን እና በኢትዮጵያ የኖርዌ ኤምባሲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ አገሮች የዘላቂ ልማት ግቦቻቸውን ለማሳካት እያካሄዱት ያለው ተግባርና እየገጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን የሚያመላክቱ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የአፍሪካ አገራት የልማት ግቦቻቸውን ለማሳካት እያካሄዱት ባለው የልማት ስራ በታዳሽ የኃይል አማራጭ ዘርፍ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተመክሯል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተገኝ ገብረ-እዚአብሔር፤ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የምሁራን ሙያዊ ምክክር እጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያስመዘገበች ያለው ስኬት የልማት ግቦቿን እውን ለማድረግ የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ስለመሆኗ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌ ኤምባሲ የትምህርት ዘርፍ አማካሪዋ ጃኒ ቤተ ሙለር፤ ኖርዌ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት በማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱም በመልካም አስተዳደር፣ በግል ዘርፍ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃና ድጋፍ እንዲሁም በግብርና ልማት ዘርፎች 85 ሚሊየን ዶላር ፈሰስ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል።

የትምህርት ተቋማትን በማገዝም ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራ በማከናወን ኢትዮጵያ የልማት ግቦቿን እውን እንድታደርግ ኖርዌ እገዛ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዳን ባኒክ፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት የልማት ግቦቻቸውን ለማሳካት የኃይል ልማታቸውን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ የአፍሪካ አገራት ዘላቂ የልማት ግቦቻቸውን እውን ለማድረግ በሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች የታዳሽ ኃይል አማራጭን ማስፋት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።

ለዚህም በኃይድሮ፣ በንፋስና በፀኃይ የኃይል አማራጭ ልማት ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም