በአዳማ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ 82 የሸኔና አሸባሪው ህወሃት ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

83

አዳማ  መስከረም 19/2015 (ኢዜአ)  በአዳማ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ 82 የሸኔና አሸባሪው ህወሃት ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፀጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የአዳማ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መኩሪያ ድንቁ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ መስቀልና ኢሬቻን ጨምሮ ህዝባዊ በዓላትን ለማወክ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ  33 የአሸባሪው ሸኔና አባ ቶርቤ አባላት ፤እንዲሁም 49 የአሸባሪው ህወሃትና ሌሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሆራ ፊንፊኔና ሆራ አርሰዲ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል የለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ መስተዳደሩ ከምስራቅ ሸዋ ዞንና አጎራባች ከተሞች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የተቀናጀ የፀጥታ አካላት ስምሪት በመስጠት የፀጥታ ሃይላትን በአንድ ላይ በከታማዋ በአራቱም መግቢያና መውጫ ቦታዎች ላይ በቅንጅት የፍተሻ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ የኢሬቻ በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፍተሻ ስራው ሙያዊ እንዲሆን የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ልዩ ሃይልን ጨምሮ መደበኛ ፖሊሶችን በማሰማራት ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም 19 ሽጉጦች፣ 6 ክላሽና ከ3ሺህ በላይ የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን ጠቅሰዋል።

እንግዶች አዳማ ከተማ አርፈው ወደ አዲስ አበባና ቢሾፍቱ የሚሄዱ በመሆኑ የፀጥታ ስራውን በመስራት ሰርጎ ገቦችን የመከታተልና የፍተሻ ስራዎችን በጋራ በመስራታችን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም