ኢትዮጵያን ሲወዱ ለሀገሩ ክብር መጠበቅ የሚዋደቅ ወታደርን መውደድ እንደሆነ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በተግባር አሳይቷል--ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

210

መስከረም 19 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ሲወዱ ለሀገሩ ክብር መጠበቅ የሚዋደቅ ወታደርን መውደድ እንደሆነ ርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በተግባር አሳይቷል ሲሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ተናገሩ።

ኮሎኔል ጌትነት ይህን የተናገሩት በአርቲስቱ የአስክሬን ሽኝት መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው መከላከያ ሚኒሰቴርን በመወከል ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በወጣትነት ዕድሜው በተለያዩ ስርዓቶች በየዘመናቸው ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ያገለገሉ ወታደሮችን የማግኘት ዕድል አግኝቷል ብለዋል።

አሁን ባለንበት ጊዜም ግንባር ድረስ ዘልቆ በሙያው ሲያገለግል ስናይ ማዲንጎ አፈወርቅ ጉዳዩ ከመጣው እና ከሄደው ጋር ሳይሆን ሀገሩን በህይወት መስዋዕትነት ከሚጠብቅ ወታደር ጋር መሆኑን ማሳያ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን መውደድ ከሆነ ከፈጣሪ በታች ጠባቂ ወታደሮችን ማክበርና መውደድ እንደሆነ ከልጅነት አእምሮው ጀምሮ ቀድሞ የገባው ከያኒ ነበርም ሲሉ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ‘ቅድሚያ ለእናት ሀገር ኢትዮጵያ’ በሚል ከሙያ አጋሮቹ ጋር በማሰልጠኛ ምልምል ወታደሮችን፤ በግንባር ደግሞ ሀገሩ እንዳትፈርስ በጀግንነት እየተዋደቀ ካለው ሰራዊት ፊት ቀርቦ በተስረቅራቂ እና አስገምጋሚ ድመጹ ሰራዊቱን አነቃቅቷል፣ አበረታቷል፣ አጀግኗል ብለዋል።

የደመራው እንጨት ወደየት ይወድቅ ይሆን ሳይል በቆራጥነት ላመነበት ሲሰራ የነበረው ጀግና የደመራ ዕለት ማረፉን ስንሰማ ብናዝንም ዘመን በማይሽራቸው ስራዎቹና የዓላማ ጽናቱ እንደ ጀግና ግንባር ላይ እንደ ወደቀ ወታደር እናከብረዋለንም ብለዋል።

ያከበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት ሁሌም ያከብረዋል፤ ሁሌም እናስበዋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ ለሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በሙሉ መጽናናትን ይመኛል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም