በኢትዮጵያ የንብረት ታክስ ስርዓትን በውጤታማነት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ህጋዊ አሰራሮች ከወዲሁ ሊዘጋጁ ይገባል

መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ የንብረት ታክስ ስርዓትን በውጤታማነት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ህጋዊ አሰራሮች ከወዲሁ ሊዘጋጁ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የንብረት ታክስን በሚመለከት የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

ውይይቱም በዋናነት በጉዳዩ ላይ የተከናወነ ጥናታዊ ጽሁፍ እና የታክስ ህግ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ የክልልና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በዚሁ ጊዜ የንብረት ታክስ ተግባራዊ መሆን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የንብረት ታክስ ለአገር ኢኮኖሚ ልማት ያለው ፋይዳ አጠያያቂ ባይሆንም በአተገባበሩ ላይ ግን የባለድርሻ አካላት ጥልቅ ውይይትና መግባባት እንደሚያስፈልግም ነው ያብራሩት፡፡

በተለይ የግብር ስርዓቱን በአጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት ትክክለኛ የጊዜ እቅድ ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው የንብረት ታክሱን በሚመለከት ቀጥተኛ የሆነ ህጋዊ አሰራር ሊበጅገለት እንደሚገባ አመልክተዋል።

"የገቢ ታክስን ማን ይሰብስብ?" የሚለው ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ አሰራሮች ከወዲሁ ሊዘጋጁ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው የንብረት ታክሱ የሚመለከታቸው የንብረት አይነቶችን በዝርዝር ተለይተው ሊቀመጡ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የንብረት ታከስ ተግባራዊ መሆን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ከማድረጉም ባሻገር አገርን በጋራ ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው ጨምረው የገለጹት፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ተግባራዊ እየሆነ የመጣው ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፤ ይህም ክልሎች ያላቸውን ሃብት ለልማት እንዲያውሉ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የንብረት ታክስን በሚመለከትም የፌደራልና የክልል መንግስትን በጋራ በሚያሰራ መልኩ ህጋዊ ስርዓቶች ሊዘጋጁ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

በተለይ ለአሰራር ስርዓት ግልጸኝነት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በመጥቀስ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤የዜጎችን ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአገሪቱን የድህነት ምጣኔ ለማሻሻል የንብረት ታክስ ተግባራዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የንብረት ታክስ አሰባሰብ ባለቤትነትን በሚመለከት በህገመንግስቱ በግልጽ የተቀመጠ አንቀጽ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ጉዳዩ ህገመንግስታዊና ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ይህን ለማድረግ በቅድሚያ የውሳኔ ሃሳብ መዘጋጀት እንዳለበት የጠቀሱት አፈ-ጉባኤው፤ከዚህ አኳያ ባለድርሻ ተቋማት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ጭምር ጉዳዩን የሚመለከት ሰነድ አዘጋጅተው ሊያቀርቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም