እንቦጭን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በማዋል ለማስወገድ እየተሰራ ነው

615

ባህር ዳር፣ መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በማዋል ማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ላይ እየተሰራ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ ኤምባሲ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር እምቦጭን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሰጥቶ ማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ላይ የአሰልጠኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው በስልጠናው ላይ እንዳሉት፣ የእንቦጭ ዘር ለበርካታ ዓመታት በመሬት ውስጥ ሳይበሰብስ የሚቆይ ሲሆን አመቺ ሁኔታ ሲያገኝም የሚስፋፋ አደገኛ አረም ነው።

“ይህን አደገኛ መጤ አረም በአንድ ወቅት በርካታ ህዝብና ማሽኖችን በማሰለፍ ማስወገድና ማጥፋት እንደማይቻል ቀደም ሲል የተከሰተባቸው አገራት ተሞክሮ ማሳያ ነው” ብለዋል።

በሀገራችን በጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃማ አካላት ላይ የተከሰተውን እንቦጭ በበዝሃ ህይወት ላይ ሰፊ ጉዳት ሳያስከትል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ጋር በማያያዝ አማራጭ የማስወገጃ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

በችግሩ ቀድመው የተጠቁት እንደ ኢንዶኔዥያ ካሉ አገራት ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ እምቦጭን ለተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ ለተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ለእንስሳት ምግብነትና ሌሎች ጠቀሜታዎች ለማዋል የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፣ ኢንዶኔዥያ እንቦጭን ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ለውጭ ምንዛሬ ማግኛ በማዋል ልምድ እንዳላት ገልጸዋል።

በሀገራችን የእንቦጭ አረም ለረጅም ጊዜ በአስቸጋሪነት የሚቀጥል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ከሀገራቸው አሰልጣኝ በማምጣት ስልጠናው እንዲሰጥ መደረጉን ገልጸዋል።

በተግባር የተደገፈው ስልጠናው አረሙን በማስወገድ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በእዚህ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎች የሚያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የራሳቸውን ህይወት ለመቀየርና ለመለወጥ መስራት እንዳለባቸው አሳስበው፣ የከተማ አስተዳደሩ ትብብር እንደማይለያቸውም አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባልና የግል አማካሪ የሆኑት አቶ አህመድ ሃሰን በበኩላቸው፣ ስልጠናው እምቦጭን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል በመሆኑ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጠናው እምቦጭን በማስወገድ፣ በምርምርና ተያያዥነት ባላቸው ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ብቻ እንዲሳተፉ መደረጉን ጠቁመው፤ በቀጣይ ሰልጣኞች የገንዘብ ብድር፣ የመስሪያ ቤታ እና የመስሪያ ማሽኖች የሚያገኙበን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡስይራ ባስኑር በበኩላቸው እንዳሉት፣ “ይሄ ስልጠና የዛሬ ወር በነበረን ውይይት የገባሁትን ቃል በተግባር ማረጋገጥ የጀመርኩበት ነው” ብለዋል።

“ስልጠናውን ለማዘጋጀት ያነሳሳን እኛ ኢንዶኔዥያውን ለኢትዮጵያውያን ያለን ስሜት ነው” ያሉት አምባሳደር አልቡስይራ፣ በእህትና ወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖረን ከመፈለግ የመነጨ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

እንቦጭን ጥቅም ላይ በማዋል በኩል ያለንን ልምድ፣ እውቀትና ክህሎት ተመሳሳይ ችግር ለገጠማት ኢትዮጵያ ብናካፍል አብሮ የመለወጥ፣ የማደግና የመልማት ፍላጎታችንን ለማረጋገጥ ያስችላል ሲሉም አክለዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ አሁን የተጀመረው ተግባር ተኮር ስልጠና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።

አምባሳደሩ ቀደም ሲል በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ባካሄዱት ውይይት የእንቦጭ አረምን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታነት ለማዋል በሚደረግ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ኢዜአ በወቅቱ መዘገቡ የሚታወስ ነው።