ኢትዮጵያ የዓለም ህዝብ ሁሉ ሊጎበኛት የሚገባ የባለብዙ አስደናቂ ቅርሶች ሀገር ሆና አግኝተናታል- የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች

157

መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የዓለም ህዝብ ሁሉ ሊጎበኛት የሚገባ የባለብዙ አስደናቂ ቅርሶች ሀገር ሆና እንዳገኟት ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ገለጹ።

በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት በተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመታደም የመጡ የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ጎብኝዎች ኢትዮጵያ ባለብዙ መልክ ሀገር ናት ይላሉ።

ፈረንሳያዊቷ ቱሪስት ዳና ኢድ ኢትዮጵያን ስትጎበኝ የመጀመሪያዋ ሲሆን በኢትዮጵውያን የባህል ልብስ አጊጣ በበዓሉ ላይ ተገኝታለች።

የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት፣ ፍቅርና አንድነታቸው የተለየ ቀልብ የሚስብ ኃይል እንዳለው ምልከታዋን ለኢዜአ አጋርታለች።

ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገራት የማይገኙ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እሴት ያሏት ሀገር በመሆኗ ሊጎበኙ ከሚገቡ ታሪካዊ ሀገሮች ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጣት ሆና እንዳገኘቻትም እንዲሁ።

በሀገሪቱ ለጎብኝዎች የሚደረገው እንክብካቤና እውነታ ላይ የተመሰረተ የመረጃ አሰጣጥም መልካም መሆኑን በማንሳት የውጭ ሀገራት ዜጎች ኢትዮጵያን ሊያዩዋት እንደሚገባ ጠቁማለች።

ከደቡብ አፍሪካ የመጣው ሳም ኬሎ እንደተናገረው በኢትዮጵያ ሰዎች የሚያሳዩት አቀባበል የእንግዳነት ስሜት ሳይሆን ነባር የሀገሪቱ ነዋሪ የሆንን ያህል ጥልቅ ስሜት የሚሰጥ ነው ይላል።

May be an image of 7 people, people standing and outdoors

አፍሪካውያን በቱሪዝም ኢንዱስትሪ እርስ በእርስ መተሳሰር እንዳለባቸው በመጠቆም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛና ምድረ ቀደምት በመሆኗ ዓለም ሁሉ መጥቶ ሊጎበኛት እንደሚገባ ነው የተናገረው።

ኢትዮጵያን እንደሚወዱ በተደጋጋሚ የተናገሩት ከአሜሪካ ፍሎሪዳ የመጡት ቱሪስት አንዲ ስቴይን በበኩላቸው ከሚወዷት ሀገር አንዷ በመሆን በተደጋጋሚ እንደሚጎበኟት ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ በተዛባ መልኩ የሚሰራጩ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ የቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚገድብ ሁኔታ አለመኖሩን አረጋግጫለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗ፣ ጥንታዊ የጥበብ አሻራዎች፣ ያለው የሰው አቀባበል፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቦታዎች በተደጋጋሚ እንዲጎበኟት ካደረጓቸው አስደናቂ መስህቦች መካከል ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ የስልጣኔ መገለጫዎች ከሆኑት አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን በምዕራባውያን ብዙም እንደማይታወቅ ገልጸው የማስተዋወቅ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

May be an image of 3 people and people standing

በተለያየ ቦታዎች ለጉብኝት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፉ መልካም ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን የተናገሩት ከኬንያ የመጡት ጆናታን ኪሉ ናቸው።

በመሆኑም የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አስደናቂ መስህቦችን ሊጎበኙ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም