አሸባሪው በስልጣን ዘመኑ ዜጎች እርስ በርሳቸው እንዲጠራጠሩና ወደ ግጭት እንዲገቡ ሲያደርግ ቆይቷል- አፈ ጉባኤው

98

ሐረር፤ መስከረም 18/2015(ኢዜአ) ፡- አሸባሪው የህወሃት ቡድን በስልጣን ዘመኑ ዜጎችን እኩል ባለማየት እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩና ወደግጭት እንዲገቡ ሲያደርግ መቆየቱን የሐረሪ ጉባኤ አፈ- ጉባኤ ሙህየዲን አህመድ ገለጸ ፡፡

 አፈ- ጉባኤው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ቡድኑ አሁን ላይም  የውሸት ፕሮፖጋንዳ እና የጠላት ተልዕኮን ይዞ  ሀገርን ለማፍረስ  እየጣረ መሆኑን  ህዝቡ ተረድቶታል ብለዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ ክልሎችን አጋር እና እህት  በሚል ከፋፍሎ ፍትሃዊ ያልሆነ አካሄድ ያራምድ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በሀገራዊ ጉዳይ ላይ አንዱ ወሳኝ ሌላው ተመልካች ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት   አቶ ሙህየዲን፤  አሸባሪው አጋር የሚላቸውን ክልሎች  በቡድኑ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ከማስፈፀም ባለፈ የመደገፍም ሆነ የመቃወም  ብሎም በሀገራዊ ጉዳይ  የመሳተፍ እድል የተነፈጓቸው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በወቅቱ ቡድኑ  በሚያንቀሳቅሳቸው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች አማካኝነት  በክልሎች በሚያደርገው  ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሞግዚት አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶ ነበር ያሉት  አፈ- ጉባኤ ሙህየዲን ፤ ይህም በመስተዳድሮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማስከተል ግፍ ሲፈጽምባቸው  መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል  የኮትሮባንድ ንግድና መሰል እንቅስቃሴዎች ለይ በቀጥታ በመሳተፍ  የክልልም ሆነ የፌዴራሉን ህገ መንግስት የሚንዱ ተግባራትን ሲያራምድ እንደነበረም አስረድተዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በሚዘውራቸው የመከላከያ አመራሮችን በመጠቀም በኮትሮባንድ ንግድ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር አመልክተው፤ በኮትሮባንድ ንግድ ተደርሶባቸው የሚያዙ  አካላትን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ድረስ በመግባት ሲያስፈታ መቆየቱንም ገልጸዋል።

 ውህድ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲቋቋም የቀረበው ሀሳብ  ላይ ውህድ ፓርቲው ፍላጎቴን አያራምድልኝም ብሎ በማሰቡ  አሸባሪ ቡድኑ  በመቃወም በእምቢኝነት  የወጣበት ሁኔታ መኖሩንም አንስተዋል።

ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍሉን በተመለከተ አጋር የሚላቸው ድርጅቶች ከተወሰነላቸው ውጪ ድምፃቸው የሚሰማበት ሁኔታ በመንፈግ ቡድኑ ሲያራምደው በነበረው ዜጎችን እኩል ያለማየት ዝንባሌ እርስ በእርሳቸው  እንዲጠራጠሩና ወደግጭት እንዲገቡ ሲደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሰላም ሲኖር   ስለሀገር  ልማት ማሰብና መስራት እንደሚቻል የተናገሩት አፈ-ጉባኤው፤  የመከላከያ ሰራዊቱ ለሀገሪቱ ወሳኙ እና የሉአላዊነት ዋስትናችን ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪ የህወሃት ቡድን በሀገሪቱ ላይ የቃጣውን ጥቃት  ሰራዊቱ በብቃት እና በላቀ ጀግንነት እየመከተ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት የሚደረገውን ድጋፍ ህዝቡን አስተባብረው በማጠናከር  በደጀንነታቸው  እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ የውሸት ፕሮፖጋንዳ እና የጠላት ተልዕኮን ይዞ ሀገርን ለማፍረስ እየጣረ መሆኑን ህዝቡ ተረድቶታል ያሉት አፈ ጉባኤው ፤ የሽብር ቡድኑንና ከኋላ የሚጋልቡትን እርቃናቸውን በማስቀረት የማጋለጥ ስራ ማጠናከር  ይገባናል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም