የሐረሪ ክልል የግል ጤና ተቋማት ማህበር ለጀግናው መከላከያ ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

65

ሐረር ፤መስከረም 18/2015(ኢዜአ) ፡- የሐረሪ ክልል የግል ጤና ተቋማት ማህበር ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግማሽ ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ማህበሩ ለሰራዊቱ ያደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ አስረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የሀገርን ሰላምና ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው  ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

በክልሉ የሚገኘው የግል የጤና ተቋም ማህበርም ሀገርን ለማዳን በተለያዩ ወቅት ለሚያደርጉት የድጋፍ ስራዎች ምስጋና አቅርበዋል።

"ሀገር ሰላም ሲሆን ነው ሰርቶ መኖር የሚቻለው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  በተለይ ማህበሩ እያከናወነ የሚገኘውን የድጋፍ ስራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ማህበሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚከናወኑ ስራዎችን  የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው ፤ ማህበሩ ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት ለሰራዊቱ በራስ ተነሳሽነት ያደረጉት ድጋፍ  የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ ድጋፉን  አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሮናን በመከላከልና በሌሎች ሀገራዊ ጥሪ ላይ ማህበሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የሐረሪ ክልል   የግል ጤና ተቋማት ማህበር  ሰብሳቢ ዶክተር ጌታሁን ደሳለኝ ናቸው።

በቀጣይም ማህበሩ በክልሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት  በሚከናወኑ ስራዎች ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም