የምርጥ ዘር እጥረትን በመፍታት መንግስት በስንዴ ምርት ላይ የያዘው እቅድ እንዲሳካ የበኩሌን እየተወጣሁ ነው - ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ

155

ጎባ መስከረም 18/2015(ኢዜአ) የምርጥ ዘር እጥረት ከማቃለል በተጓዳኝ መንግስት ስንዴን ወደ ውጪ ለመላክ የያዘው እኒሼቲሽ እንዲሳካ የበኩሉን እየተወጠ መሆኑን የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘርን ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ ማህበራዊ ሃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑም ተመላክቷል።

በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጫላ አበበ እንደገለጹት “ኢንተርፕራይዙ በዋናነት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው”፡፡

በዚህም በመኽር አዝመራው ከ17 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተለያዩ ምርጥ ዘር እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተባዛ ካለው የምርጥ ዘር መካከል የዋግ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡና ከተለያዩ የግብርና ምርምር ማዕከላት ተገኝተው በኢንተርፕራይዙ የተባዙ የስንዴ፣ የገብስና ባቄላ ዝርያዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በኢንተርፕራይዙ ስር በሚገኙ ሰባት የእርሻ ማሳዎች እየተባዙ ከሚገኙት ምርጥ ዘር ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አመልክተዋል።

ስራ አስኪያጁ እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ መንግስት ስንዴን በመስኖ ለማልማት የያዘውን ዕቅድ በምርጥ ዘር አቅርቦት እየደገፈ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ለመጀመሪያው ዙር የመስኖ ወቅት ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር መዘጋጀቱን በማሳያነት አቅርበዋል።

ኢንተርፕራይዙ በተለይ መንግስት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ የያዘው ግብ እንዲሳከ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ ለማዘጋጀት አቅዶ እየሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ስራ አስኪያጁ እንዳሉት ምርጥ ዘር ማባዛትና ማሰራጨት ብቻውን ግብ አለመሆኑን ጠቁመው በዘር ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በሌሎች ተዛማጅ ተግባራት የተሻሻሉ አሰራሮች ላይ በባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን ለሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጥም አስረድተዋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ከምርምር ተቋማት የተቀበለውን ዘር በራሱ ማሳ ላይ ካባዛ በኋላ አዋጭነታቸውን በመገምገም ከሙያዊ ምክር ጋር ለአርሶ አደሩና ሌሎች ተጠቃሚዎች ያሰራጫልም ነው ያሉት፡፡

ከኢንተርፕራይዙ ድጋፍ ከተደረገላቸው የምዕራብ አርሲ አዳባ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ጡባ ሀሰን እንዳሉት ምርጥ ዘር በወቅቱና በሚፈልጉት መጠን ማግኘታቸው ምርታማነታቸው እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደር አብደላ ማህሙድ በበኩላቸው ከኢንተርፕራይዙ የሚቀርብላቸውን ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የአካባቢውን ዝርያ በመጠቀም በሄክታር ያገኙ የነበረው የስንዴ ምርት ከ15 ኩንታል እንደማይበልጥ ገልጸው  ምርጥ ዘር  መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ የቀድሞውን ሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ እንደቻሉ  ጠቅሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በዞኑ የሚገኙ የሮቤና ሲናና እርሻዎችን ጨምሮ በምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ የሚለማ መሬት ያስተዳድራል።

ከዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የእርሻ ማሳዎች ለምርጥ ዘር ብዜት እንደሚውል ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም