የሶማሌ ክልል ህዝብ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በቁጥር ከ1ሺህ 2ዐዐ በላይ የእርድ እንስሳት ድጋፉ አደረገ

156

ጅግጅጋ ፤ መስከረም 18/2015(ኢዜአ)፡- የሶማሌ ክልል ህዝብ አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በግንባር እየተፋለመ ላለው ለጀግናው የሀገርን መከላከያ ሠራዊት በቁጥር ከ1ሺህ 2ዐዐ በላይ የእርድ እንስሳት ድጋፍ አደረገ።

ለሠራዊቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከህዝቡ የተደረገው  የእርድ እንስሳት ድጋፍ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት በክልሉ ፋፈን ዞን ሸበሌ ወረዳ ዛሬ  ተካሂዷል።

 ከክልሉ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የፍየልና በግ ሙክቶች  አሰባሳቢ የሽማግሌዎች ሸንጎ ሰብሳቢ ገራድ ኩልሚዩ ገራድ መሀመድ ናቸው።

ሰብሳቢው  በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ "ለመከላከያ ሠራዊታችን ድጋፋችንን ለማስቀጠል ሁሌም ደጀንነታችንን እናረጋገጥለን "ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የማይፈልጉ የውስጥና የውጪ ጠላቶችን በመደምሰስ በዱር በገደሉ ከፍተኛ መስዋትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጎኑ መቆሙን  ለማሳየት መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከ10 ሚልየን ብር በላይ የሚገመተው  ይሄው ድጋፍ በቀጣይ ለሠራዊቱ እንደሚላክ የተናገሩት ገጋድ ኩልሚዬ፤  ድጋፉን ለሰጡ አካላት ምስጋና አቅርቦዋል።

የክልሉ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ የሀገር ሉዓላዊነት በማስከበር  ላይ ለሚገኙት ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፉን  አጠናክረው እንደሚቀጥል ገራድ ኩልምዬ አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሃት ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የአገዛዝ ዘመን በሶማሌ ህዝብ  ላይ ከፍተኛ ጭቆናና በደል ማድረሱን አስታውሰው፤   የሽብር ተግባሩ  በምንም ታምር እንደማይሳካ ነው የገለጹት።

በቅርቡ አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን በሶማሌ ክልል ጥቃት ለመሰንዘር በሞከረበት  ወቅት የክልሉ ህዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች አርአያነት እንዳለው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም