አዲሱ ስርአተ ትምህርት ለተሻለ የትምህርት ጥራትና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ ነው- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ስርአተ ትምህርት ለተሻለ የትምህርት ጥራትና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ ነው- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) ዘንድሮ የጀመረው አዲሱ ስርአተ ትምህርት ለተሻለ የትምህርት ጥራት፣ በተግባር ተኮር እውቀት በመደገፍ ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና እንደሚኖረው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
በአዲስ አበባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩ ይታወቃል።
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ከ9 እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ በሁሉም ክልሎች በሙከራ ደረጃ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
አዲሱን ሰርአተ ትምህርት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ትምርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ በብዙ መልኩ ለአገርና ለዜጋ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን አብራርተዋል።
አዲሱ ስርአተ ትምህርት ለተሻለ የትምህርት ጥራት፣ በተግባር ተኮር እውቀት በመደገፍ ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና የሚኖረው መሆኑንም ተናግረዋል።
የመማሪያ መፅሃፍት ዝግጅትን በተመለከተም በሂደት እየበለፀገ የሚሄድ መሆኑን ጠቅሰው በአፈፃፀም ሂደት ለትምህርት ጥራት የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።
"የመማር መሰረተ ሃሳቦች ለማወቅ፣ ለመስራት፣ ለአብሮነት፣ ሆኖ ለመገኘት" መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው እነዚህን ነጥቦች በአግባቡ ጨብጦ የሚራመድ ትውልድ ለማፍራት የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በአዲሱ ስርአተ ትምህርት የብዝሃ ቋንቋ ባለቤት፣ በስነ ምግባር የታነፀና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በትግበራው ሂደት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የትምህርት ቤቶች የሰው ሃይልና የመማርያ ክፍል ማሟላት ስለሚኖርባቸው ለዚህም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።