የ10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮች ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

140

መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) የጃፓን መንግስት 185 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮችን ድጋፍ ለማድረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ፡፡

የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ተፈራርመዋል።

ክሊኒኮቹ ተንቀሳቃሽና ሙሉ የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎችን የሚያሟሉ መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፤ የጃፓን መንግስት 10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮችን በ185 ሚሊዮን ብር ገዝቶ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡   

በኢትዮጵያ በተለይም የእናቶችንና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ድጋፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የህክምና ክሊኒኮቹም በአምስት ክልሎች ከ800 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው፤ ዘመናዊ መሳሪያ የሚገጠምላቸው የህክምና ክሊኒኮቹ ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የምታደርገውን እንቅስቃሴ የሚያግዙ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በተለይም በአርብቶ አደሮች አከባቢ የሚኖሩ እናቶችና ህጻናትን ጤና ለማሻሻልም ያላቸው አስተዋጽኦ ክፍተኛ መሆኑን ገልጸው የጃፓን መንግስት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡  

የጤና ሚኒስትር ዶክትር ሊያ ታደሰ፤ በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በተለይም የእናቶችና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ አከባቢዎች የህክምና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ከጃፓን መንግስት የተገኘው ድጋፍ ይህን ክፍተት ይሞላል ብለዋል።

በአርብቶ አደር አከባቢዎችና በተለያዩ ሁኔታዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የህክምና ተደራሽነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የጃፓን መንግስት ከዚህ ቀደምም ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ አጋርነቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም