የአፈር አሲዳማነትን ማከም ከተቻለ እስከ 71 በመቶ የምርት ዕድገት ማግኘት እንደሚቻል ተገለጸ

107

አዳማ መስከረም 18/2015 /ኢዜአ/ የአፈር አሲዳማነትን ማከም ከተቻለ እስከ 71 በመቶ የምርት ዕድገት ማግኘት እንደሚቻል ተገለጸ።

የግብርና ሚኒስቴር የግል ዘርፉን ያማከለ የአፈር አሲዳማነትን ለማከም የኖራ አቅርቦትና ስርጭት የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ውብሸት እንደገለፁት በሀገሪቷ እየታረሰ ካለው ጠቅላላ መሬት ውስጥ 41 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሳዳማነት መጥቃቱን ገልጿል።

ከዚህ ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነው የእርሻ ማሳ በከባድ አሲዳማነት መጠቃቱን ጠቅሰው ችግሩን ለማቃለል የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል።

በተለይ የግሉን ዘርፍ ያማከለ የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ በኖራ አጠቃቀምና ውጤታማነት ላይ ያለውን ግንዛቤ ከማዳበር ጀምሮ የቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልሎችና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየታረሰ ያለው 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መሆኑን የገለፁት አቶ መንግሥቱ ጠቅሰዋል።

የአፈር አሲዳማነት መጠኑ ከ5 ነጥብ 5 በመቶ በላይ በሆነ የእርሻ ማሳ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ምርትና ምርታማነት ይቀንሳልም ብለዋል።

በጀርመን ልማት ትብብር ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) የአፈር ለምነት ማሻሻያ ፕሮጀክት የቴክኒክ አማካሪ አቶ ውብሸት ደምሴ በበኩላቸው በከፍተኛ አሲድ የተጠቃው የእርሻ ማሳ ምርትና ምርታማነት ከ50 እስከ 100 በመቶ ምርት ይቀንሳል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የምርት ማሳደግያ ግብዓት በተለይ የአፈር ማዳበሪያ ውጤታማ እንዳይሆን በማድረግ በአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብለዋል።

ስንዴ፣ ገብስ፣ ቦቆሎና ባቄላ የሚታረስባቸው ማሳዎች በዋናነት በአፈር አሲዳማነት የሚጠቁ መሆናቸውን ጠቅሰው የእርሻ ማሳውን በኖራ ማከም ከተቻለ እስከ 71 በመቶ የምርት ዕድገት ማግኘት እንደሚቻል ገልጿል።

በዚህም በቅርቡ በዘርፉ በተካሄደው ጥናት በኖራ ከታከመ መሬት በሄክታር ስንዴ 47 ኩንታል፣ ገብስ 43 ኩንታል፣ ባቄላ 39 ኩንታል እንዲሁም ቦቆሎ 51 ኩንታል መገኘቱን መረጋገጡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም