አዲሱ አመት በአንድነትና በህብረት ለአገር ሰላም የምንሰራበት ሊሆን ይገባል

299

መስከረም 17/2015 (ኢዜአ) አዲሱ አመት በአንድነትና በህብረት ለአገር ሰላምና እድገት የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የደመራ በአል ታዳሚ ወጣቶች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ሞትንም ድል አድርጎ የሰውን ልጅ ድህነት ላወጀበት መስቀል ልዩ ኅይማኖታዊ ትዕምርትነት ትሰጠዋለች።

በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ የተቀበረውን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መሰቅል ከ3 መቶ ዓመታት በኋላ መገኘቱን በማስመልከት ነው የደመራ በዓል በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የደመራ በአልን ለመታደም የመጡ የዕምነቱ ተከታይ ወጣቶች የመስቀል በአል ፍቅርና አንድነትን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የመስቀል በአል በኢትዮጵያ የሚከበረው በአዲሰ አመት መጀመሪያ በመሆኑ ለሰው ልጅ ያሳየውን ፍቅርና አንድነት በተግባር ለማሳየት የምናቅድበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አዲሱ አመት በእለት ተእለት ህይወታችን የጠፋውን ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም ፈልገን የምናገኝበት ለአገር እድገት የምንሰራበት ሊሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

አገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትዘልቅና የምትጸና በመሆኑ ከአባቶቻቸው የወረሱትን ሃይማኖታዊ ትኡፊትና አገራዊ አንድነት ለማስቀጠል ጠንክረው የሚሰሩበት አመት እንደሚሆንም አክለዋል።

የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ማህበራዊ ሚዲያንና ሌሎች የመከፋፈያ መንገዶችን በመጠቀም የአገርን ቀጣይነት ለማሰናከል የሚሰሩ አካላትን ወጣቱ በአስተውሎት ሊያቸው ይገባል ሲሉ መክረዋል።

ቀደምት አባቶች በሃይማኖት፣ በስነ-ህንጻ፣ በምጣኔ ሃብት እድገት ያስቀመጡትን አሻራ በማስቀጠል አሁን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።

ህብረት ያለውን ሃይል በመረዳት ለአገር እድገት፣ ሰላምና ብልጽግና ይምንሰራበት አመት ሊሆን ይገባል ብለዋል ወጣቶቹ።

በኦርቶዶክስ እምነ ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል በአል ወጣቶች፣ ህጻናት፣ አዛውንቶች፣ የውጭ አገር ጎብኝዎች በድምቀትና በአንድነት የሚያከብሩት ሃይማኖታዊ በአል ነው።