ዞኖቹ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

219

መቱ/ጂማ መስከረም 17/2015 (ኢዜአ) የኢሉባቦር ዞንና ጂማ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድርጋቸውን ገለጹ።

የኢሉባቦር ዞን ዋና አሰተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ዞኑ አንድም ተማሪ በአቅም ማጣት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይስተጓጎል እየተሰራ ነው።

በዞኑ ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችና አልባሳት ድጋፍ የተደረገ መሆኑን በመግለጽ።

ድጋፉ የተደረገው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልና በሌሎችም በዞኑ በሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አማካኝንት መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ ከተለያዩ ሴቶች አደረጃጀቶች፣ ከባለሀብቶች፣ ከነጋዴዎችና ከመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ወጣቶች ጭምር እንደተሰበሰበ ጠቅሰዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል በመቱ ከተማ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አብራሃም ምሬሳ ለተደረገለት ድጋፍ አመስግኖ ትምህርቱን በትኩረት ተከታትሎ ጥሩ ደረጃ ለመድረስ እንደሚያበረታታው ነው የተናገረው።

ሌላኛው ተማሪ ዮሐንስ ታደሰ የሚረዳው እንደሌለና ትምህርቱን በዚሁ መልክ በሚያገኘው ድጋፍ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

የተደረገለት ድጋፍም የበለጠ በትምህርቱ እንዲጠነክር የሚያግዘው መሆኑን ነው የተናገረው።

በተመሳሳይ የጂማ ከተማም 520 ለሚሆኑ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች አንድ ደርዘን ደብተር፣ እስኪቢርቶና እርሳስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የተሰበሰበው ከጅማ ዩኒቨርሲቲ  ሰራተኞች፣ ከ'አባ ገዳ ማህበር'፣ ከጅማ ከተማ ወጣቶች መሆኑም ታውቋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ እንዳሉት ሰራተኞቹ ካላቸው ቀንሰው ድጋፍ ያደረጉ በመሆኑ አመስግነዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ አክለውም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ምን ጊዜም የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚተጋ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ተማሪዎችንና ወላጆችን ማገዝና ከጎናቸው በመቆም አሰፈላጊ በመሆኑ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች መደገፋቸው ይበረታታል ብለዋል።

የጅማ ከተማ ወጣቶችና በአባ ገዳ ማህበር ያደረጉት ድጋፍ 82 ሺህ ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ መሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም