ለመተከል ከተማ ሠላም ዘላቂነት ባህላዊ እሴቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል – አቶ አሻድሊ ሃሰን

188

አሶሳ መስከረም 17/2015 (ኢዜአ) ለመተከል ከተማ ሠላም ዘላቂነት ባህላዊ እሴቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

የሽናሻ ብሄረሰብ አባቶች ባህላዊ እሴቶች በመጠበቅ ያደረጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩም ርዕሰ-መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሽናሻ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጋሪ-ዎሮ” ዛሬ በአሶሳ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርዓት ተከብሯል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በመተከል ዞን ለተገኘው ሠላም የሽናሻ ብሄረሰብ ታላላቅ አባቶች ያደረጉት አስተወጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ጋሪ-ዎሮ የሰላም በዓል መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ባህላዊ እሴቶችን መሠረት በማድግ አሁን በዞኑ የተገኘውን ሠላም ለማስቀጠል ርብርብ እንደሚያስልግ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ረገድ ከብሄረሰቡ የሃገር ሽማግሌዎች በተጨማሪ ወጣቶች እና ሌሎችም ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ በበኩላቸው የሽናሻ ብሄረሰብ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ሊሠራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የቦሮ ሽናሻ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታየ ቡሎ በበኩላቸው የጋሪ ዎሮ በዓል የተጣላ እንዲታረቅ እና ሁሉም በይቅርታ ወደ አዲስ ዘመን የሚሸጋርበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በብሄረሰቡ ባህል መሠረት ችቦ በመለኮስ እና የእርድ ስነ-ስርዓት በማካሄድ የተከበረ ሲሆን አዲሱ ዘመን የሠላም፣ የፍቅር እና የስኬት እንዲሆን በብሄረሰቡ የሃገር ሽማግሌዎች ምረቃት ተካሂዷል፡፡

በተጨማሪም መሰል ባህላዊ እሴቶችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል፡፡

በበዓሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የብሄረሰቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡