የመስቀል በዓልን ስናከብር አንድነትን ለማስጠበቅ ቃል በመግባት መሆን አለበት - አቡነ ሰላማ

165

መተማ/ ሰቆጣ ፤መስከረም 17/2015 (ኢዜአ) የመስቀል በዓልን ህዝበ ክርስቲያኑ ሲያከብር የሌላቸውን በማሰብ የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማስጠበቅ ቃል በመግባት ሊሆን እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ተናገሩ።

የመስቀል በዓል በምዕራብ ጎንደርና በዋግኽምራ አስተዳደር ዞኖች ዋና ከተሞች በድምቀት እየተከበረ ነው።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሰላማ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መስቀል የሰላም፣ የአንድነት እና የፍቅር ምልክት ነው።

የመስቀል በዓል ሲከበርም ምዕመኑ የጠላቻ ግድግዳን በማፍረስ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት መንፈስን በማጎልበት መሆን እንዳለበት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ባለፉት ዘመናት የተሰራውን በዘርና በጎሳ የመከፋፈል ሴራ በማክሸፍ ለአንዲት ኢትዮጵያ በፍቅር፣ በይቅርታና በአንድነት መቆም አለብን ብለዋል።

ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ያሉትንና የሌላቸውን በማሰብና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም አቡነ ሰለማ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል በዓል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላ ዓለም በመሆኑ ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ያሉት ደግሞ የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ይግለጥ አበባው ናቸው።

በዓሉን ከማክበር ጎን ለጎን የውጭና የውስጥ ጠላትን መመከት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ በመሆኑ ፀጉረ ልውጦችን መከታተልና አካባቢን ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የመስቀል በዓልን ስናከብር በአሸባሪው ቡድን የተቃጣብንን ሶስተኛ ዙር ጦርነት እየመከትንና በልማት ስራዎችም ስኬቶችን እያስመዘገብን መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ በድምቀት መከበሩን ቀጥሏል።

የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ በርናባስ፤ "ሁሉም ምዕመን ለሀገሩ አንድነትና ሉዓላዊነት በአንድነት መጽናት አለበት" ብለዋል።

የመስቀልን በዓል ሲያከብርም መላ ምዕመኑ የሰላም እና የፍቅር ሰው በመሆን አሁን ሀገሪቱ  የገጠማትን ችግር ለመፍታት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መላሽ ወርቃለማው፤ ባለፈው ዓመት በህወሃት ወረራ ምክንያት የመስቀል በዓልን በአደባባይ አለመከበሩን አስታውሰዋል።

"ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በከፈለው መስዋዕትነት ዘንድሮ የመስቀል በዓልን ባማረና በደመቀ ሁኔታ በነፃነት ለማክበር በቅተናል" ብለዋል።

መላ ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ለሃገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠበቅበትን የደጀንነት ሚና እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል በዓል ዛሬ በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ የሚገኝ የኢትዮጵያውያን የጋራ በዓል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም