የመስቀል ደመራ በዓልን ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊት በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል - የኃይማኖት አባቶች

282

መስከረም 17/2015/ኢዜአ/ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊት በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።

ኢየሱስ ክርቶስ የሰውን ልጅ ከመርገምት ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤ በመስቀልም ተሰቅሎ ዲያቢሎስን ድል ነስቶ ነፍሳትን ከሲዖል እንዳወጣ መፅሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ሞትንም ድል አድርጎ የሰውን ልጅ ድህነት ላወጀበት መስቀል ልዩ ኅይማኖታዊ ትዕምርትነት ትሰጠዋለች።

በተዓምራዊነቱ ትልቅ ክብር ከሚሰጠው መስቀል ጋር የተያያዘው የቤተ ክርስቲያኗ አስተምሮ መሰረት ከሚከወኑ የትዕምርተ መስቀል ክዋኔዎች መካከል አንዱ ደመራ ነው።

ደመራ አይሁዳዊያን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መሰቅል በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመቅበራቸው ከ3 መቶ ዓመታት በኋላ የተገበኘበት ዕለት ጋር የተያያዘ ነው።

ክርስቲያኖች በየዓመቱ መስከረም 16 'ትዕምርተ መስቀል'ን የሚከወነውን ደመራ ጨምሮ የመስቀል ክብረ በዓልን "የሰላምና የደህንነት ቀን" በማለት በመልከ ብዙ መንፈሳዊና ተውፊታዊ ክዋኔዎች ይዘክሩታል።

ከቤተክርስቲያኗ የደመራ ክዋኔዎች መካከል ኃያማኖታዊ የዘማሪያን በሽብሸባ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ ወረብ፣ ዜማ፣ በደመራ ችቦ ልኮሳና ልዩ ልዩ ማራኪ የአደባባይ ትዕይንቶች ይጠቀሳሉ።

ይህን ክብረ በዓል ከአገር ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመን ባሻገር ከመላው ዓለም ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌሎች እምነት ተከታይ ጎብኚዎች በጋራ ታድመው ያከብሩታል።

ደማቁ የመስቀል ደመራ የአደባባይ ክብረ በዓል ከቅርብ ዓመታተ በፊት ከኢትዮጵያ አልፎ በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም ወካይ ቅርስነት ተመዝግቧል።

በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደበባባይ የደመራን በዓል የታደሙ የኅይማኖት አባቶች ለኢዜአ እንደገለጹት የመስቀል ደመራን ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊት በማስጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል።

የሰላም ምልክት የሆነውን የመስቀል በዓል ከኃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱ ባለፈ ታሪካዊ ሥርዓተ ቀኖና፣ ትውፊትና ቅርስነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሰላምና የምህረት ምሳሌ የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል በደምቀትና በተውህቦ ያከብሩታል።

ኢትዮጵያዊያን በመተሳሰብና በመከባበር በአደባባይ የሚያከብሩት የመስቀል በዓልም የአንድነታቸው ማሳያና መገለጫ እንደሆነ የኃይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የመስቀል ደመራን የአንድነትና ሰላም ምሳሌነት በመገንዘብ የአገራቸውን አንድነት ማስቀጠል እንዳላበቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆኑ መሰል የአደባባይ በዓላት ሲከበሩም ከመከፋፈልና መገፋፋት በመራቅ በአንድነትና በሰላም አክብሮ ማሳለፍ እንደሚገባ መክረዋል።

የኃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የውጭ ዜጎች በተገኙበት በድምቀት የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም