ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ አይተናል – ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበዓሉ ታዳሚዎች

174

መስከረም 17/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ አረጋግጠናል ሲሉ በዓሉን የታደሙ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

የመስቀል ደመራ በዓል ከአገር ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመን ባሻገር ከመላው ዓለም ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌሎች እምነት ተከታይ ጎብኚዎች በጋራ ታድመው የሚያከብሩት የአደባባይ በዓል ነው።

በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም ወካይ ቅርስነት ተመዝግቧል።

በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደበባባይ የደመራን በዓል የታደሙ በውጭ አገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የደመራ በዓል እንደስሙ የአንድነት በዓል መሆኑን በሚገባ ማስተዋላቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአሉን ከ26 ዓመታት በኋላ በአገራቸው ተገኝተው ያከበሩት ኑሯቸውን በጣሊያን አገር ያደረጉት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጸደይ ተፈራ የበዓሉ ትዕይንት አኩሪ መሆኑን ተናግረዋል።

የደመራ በአል ሃይማኖታዊ ስርአቱንና ትውፊቱን ጠብቆ ዛሬም የቀጠለ መሆኑን ከሃይማኖታዊ ስርአቱና ከምዕመናን አንድነት መረዳታቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያውያን በውጭው አለም እንደሚባለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መከፋፈላቸውን ሳይሆን መገለጫችን የሆኑት የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመከባበርና መቻቻል እሴቶች ጎልተው መታየታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

እነዚህን እሴቶች በማጠናከር ብሔር፣ ቀለም፣ ሃይማኖትና ሌሎች አጥሮች ሳይገደቡ ጠንክሮ በመስራትና ሰላምን በማስጠበቅ ኢትዮጵያ አንድነቷን አስጠብቃ የምትዘልቅ አገር መሆኗን ለአለም ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል።

ለዚህም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጋራ ቆመው ችግሮችን በጋራ ማለፍ እንደሚገባ በመግለጽ ለአገር ገጽታ ግንባታ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ሌላው ከ34 አመት በኋላ በበአሉ ላይ የተገኘው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ የደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ስርአቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ መሆኑን መታዘቡን ገልጿል።

ኢትዮጵያን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል አንድነቷን ለማዳከም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ቢኖሩም በኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት ከመቸውም ጊዜ በላይ እየጎላ መሆኑን ታዝቢያለሁ ብሏል።

አንድነት የሁሉም መሰረት በመሆኑ አንድነትን አሁንም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ድምጻዊ ሻምበል አስገንዝቧል።

አገር ጸንታና ተከብራ የምትኖረው ሁሉም በያለበትና በየተሰማራበት ዘርፍ አሻራውን ሲያሳርፍ በመሆኑ የሚጠበቅባቸውን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ትውልደ ኢትዮጵያውያኖቹ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀደመ ስሟን መልሳ አንድነቷ የተጠበቀችና የተጠናከረች አገር አንድትሆን በልማት ስራ ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።