የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር ክፉ አስተሳሰብንና ጥላቻን በማራቅ ሊሆን ይገባል-አቡነ ዮሴፍ

101

ሀዋሳ  መስከረም 17/ 2015(ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር ክፉ አስተሳሰብንና ጥላቻን በማራቅ ሊሆን እንደሚገባ የሲዳማ ክልል፣ ጌዴኦ ዞን፣ አማሮ እና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ዮሴፍ ተናገሩ።

የመስቀል ደመራ በዓል ምዕመናንና የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በሃዋሳ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የሲዳማ ክልል ጌዴኦ ዞን አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ዮሴፍ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት በዓሉ ሰውና እግዚአብሔር የታረቁበት መሆኑን ተናግረዋል።

መስቀል ለብዙ ጊዜ ቢሸሸግም በብርቱ ፍለጋ ተገኝቶ የእረፍት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

''ጨለማ ሃይል የሚያገኘው ብርሃን እስኪመጣ ውሸትም አቅም የሚኖረው እውነት እስኪገለጥ ነው'' ያሉት አቡነ ዮሴፍ፣ "መስቀሉ ሲገኝ ጨለማና ክፉ ሥራ እንደተሸነፈ ሁሉ በዓሉን ስናከብር ክፉ አስተሳሰብንና ጥላቻን በማራቅ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

"ከፈጣሪ የተሰጠችን አንዲት ሀገር ነት" ያሉት አቡነ ዮሴፍ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ተሸርበን ጥላቻን ማንገስ ፍጹም ተገቢ አይደለም ብለዋል።  

በመካከላችን የሰፈነውን ጥላቻ በማስወገድ የተሰጠችንን ሀገር ለማጽናት የእውነትና አንድነት መርህን መከተል እንደሚገባም አቡነ ዮሴፍ ተናግረዋል።

"መስቀል ብርሃን እንደመሆኑ በዓሉን በይቅርታ፣ ካለን በማካፈል እንዲሁም ሰላማችንና አንድነታችንን ሊያጠናክሩ በሚችሉ ድርጊቶች ልናከብር ይገባል" ብለዋል መክረዋል።

የጥፋት ሀይሎችን ሴራና ተግባር በመረዳት ራስንና ሀገርን መታደግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ካንቲባ ረዳት ፕሮፌሴር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፣ በርካታ ብሔረሰቦች አዲስ ዓመታቸውን በተቀበሉበት ማግስት በዓሉ መከበሩ ልዩ ደስታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የመስቀል ደመራ ካሉት እሴቶች አንድነትና ሕብረት ዋንኛ መሆኑን ያነሱት ካንቲባው ''እኛን ለመፈታተን ለሚፈልጉ ሁሉ መልሳችን ሕብረትና እውነት ነው'' ብለዋል።

"የህዝብን አንድነት፣ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል እንዲቻል አባቶች በጸሎት፣ ምዕመኑ ሰላምን በመስበክ፣ መሪዎች ደግሞ በቅን ልቦና ለሰላም በመስራት በጋራ መረባረብ ይገባናል" ሲሉም ተናግረዋል።

"የመስቀል በዓል የክርስቶስን መከራ የምናስብበትና ለሌሎች ዋጋ መክፈልን የምንማርበት ነው" ያሉት ደግሞ ሊቀ መምህር ሀብተማሪያም ጌታሰው መስቀሉን ናቸው።

በመሆኑም በዓሉን ከመታደም ባለፈ መሰባሰባችንን መልካም ነገሮችን ለማጎልበት መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዓሉን አቅመ ደካሞች በማሰብ በጋራ ማክበር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ ሸዋፀሐይ አሳልፍ በበኩላቸው፣ መስቀሉን የምንከተል ሁላችንም እርስ በርስ በመከባበር፣ በመደጋገፍና በአብሮነት በዓሉን ማክበር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም