ኦህዴድ ስያሜውን ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ቀየረ

125
ጅማ መስከረም 10/2011 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ/ በጅማ እያካሄደ ባለው 9ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ስያሜውን ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ቀየረ። ድርጅቱ  በተለያዩ የአመራርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉትን 14 ነባር አመራሮችንም በክብር አሰናብቷል። እነዚህም ፡- አቶ አባዱላ ገመዳ አቶ ጌታቸው በዳኔ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ አምባሳደር ግርማ ብሩ አምባሳደር ድሪባ ኩማ አቶ እሸቱ ደሴ አቶ ተፈሪ ጥያሩ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ አምባሳደር ደግፌ ቡላ አቶ አበራ ኃይሉ አምባሳደር  ሱሌይማን ደደፎ አቶ ኢተፋ ቶላ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው አምባሳደር ጊፍቲ አባሲያ ናቸው። በተጨማሪም ድርጅታዊ ጉባዔው በዛሬው ውሎው ለ9ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የቀረበውን ሪፖርት እንዲሁም የኦዲትና ቁጥጥር ሪፖርት ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። በውይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድና ምክትል ሊቀ መንበሩ አቶ ለማ መገርሳ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት ማብራሪያም፥ "ኦሮሞ አሸንፏል የሚባለው በዚህ ሀገር ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ ሲረጋገጥ ብቻ ነው" ብለዋል። አሁን በተገኘው ድል ላይ ከመጣላት ይልቅ አዲስ ድል ለማስመዝገብ መስራት ላይ ትኩረት መስጠት ወሳኝ መሆኑንም ዶክተር አብይ አስታውቀዋል። ከወሰን ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄም የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት ምላሽ  የወሰን ጉዳይ ወሰንን በመስመር በመለየት ሳይሆን በህዝብ መግባባት የሚፈታ ነው ብለዋል። በተለያየ አቅጣጫ ተቀምጦ ጠንካራ ድርጅት መሆን አይቻልም ያሉት አቶ ለማ  ለህዝብ ጥቅም ሲባል አላማችንን በማወቅ በንፅህና ልንታገል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። የፖለቲካ አመለካካት ልዩነት ቢኖርም ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቻቻል በሰላማዊ መንገድ መታገል ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አለመሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ድርጅታዊ ጉባዔው  በከሰዓት ውሎው የኦህዴድ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ያቀረበው ሪፖርት ላይ በመወያየት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ በትናንትና ከሰዓት ውሎውም የ9ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርት አድምጦ ማጽደቁ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ ጉባዔው በትናንትናው የሰዓት ውሎው የፕሬዚዲየም ኮሚቴ አባላት ምርጫንም አካሄዷል። በዚህም መሰረት የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኦህዴድ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኦህዴድ ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የፕሬዚዲየም ኮሚቴ አባላት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም