የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በድምቀት ተከበረ

171

መስከረም 16/2015 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን በድምቀት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉበኤ አባላትን ጨምሮ  የእምነቱ አባቶችና ተከታዮች ታድመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደራሴ አባ ተስፋዬ ወልደማሪያም በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉን ስናከብር በደልን በምህርትና ይቅርታ በማለፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

መለያየትን በመተው እርስ በርስ በመዋደድና በመከባበር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የመስቀል በዓል ትርጉም የሚኖረው ለይቅርታ፣ ፍቅርና ሰላም መኖር ስንችል ነው ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

የበጎነትና ቅንነት አስተሳስብን በማጎልበት “የሰዎች ስቃይ እንደራሳችን የሚሰማን ልንሆን ይገባናል” በማለት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የተቸገሩና አቅም የሌላቸው ዜጎችን በመደገፍ ወገናዊ አለኝታነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን ነው ያሉት፡፡