የመስቀል ደመራ በዓል ለህዝቦች መቀራረብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው-ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ

111

መስከረም 16 / 2015 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል ለህዝቦች መቀራረብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ይህን ንግግር ያደረጉት በአዲስ አበባ እየተከበረ በሚገኝው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

ሚኒስትሩ አክለውም በዓሉ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን እንዳስተላለፉልን ከጨለማው ወደ ብርሃን መሸጋገራቸንን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

በዓሉ የጥል ግድግዳ ተንዶ የዕርቅ ስርዓት የሚከናወንበት ታላቅ በዓል ነውም ሲሉ ገልጸዋል።የመስቀል በዓል በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ሰዓት በጋራ የሚከበር እንደመሆኑ መስቀል የሁሉም የጋራ ዕሴት መሆኑን ያመላክታል ።

ይህ አኩሪ እሴት በሌሎች የዓለም አገራት በብዛት የማይስተዋል በመሆኑ ጎብኚዎችን በመሳብ በኩል ሚናው ትልቅ እንደሆነም ገልጸዋል።

መስቀልን የመሰሉ አይተኬ በዓላት በሚገባ እንዲጠኑ እና ለላቀ ፋይዳ እንድንጠቀምባቸው ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ለበዓሉ ታዳሚዎች እና በየአካባቢ በአሉ ለሚያከብሩ ምዕመናን መልካም በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም